እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
08:28:31 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ኢኮኖሚ

ማሽላ -ሌላው ታላሚ ሰብል

2 ደቂቃ ንባብ
ማሽላ -ሌላው ታላሚ ሰብል
ማሽላ በአገሪቱ ከሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በመሸፈን 25 ሚሊዮን ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የገቢ ምንጭና የምግብ ዋስትና የሆነ ሰብል ነው፡፡

ማሽላ ድርቅን ተቋቋሚ ሁለገብ አገልግሎት መስጠት የሚችል ሰብል ነው።በተለያዩ መልኮች ተዘጋጅቶ ለሰውና ለእንስሳት ምግብነት ይውላል።

ሰብሉ በእስያና አፍሪካ አገሮች ለሚገኙ ሕዝቦች ዋነኛ ምግብ ሆኖ ያገለግላል።

ሰብሉ በሞቃት፣በረሃማና ሌሎች ሰብሎች በማይበቅሉባቸው ከፍተኛ ቦታዎችም መብቀል ይችላል፤በተለይም ድርቅን የመቋቋም አቅሙም ከፍተኛ እንደሆነም መረጃዎች ያሳያሉ።

በዓለም ላይ ታዋቂነት ያገኙ 25 ዓይነት የማሽላ ዝርያዎች አሉ።

ዝርያዎቹ በሚሰጡት አገልግሎት ተመድበዋል።እነርሱም፦ የምግብ(Grain Sorghum)፣የመኖ(Forage Sorghum)ና ጣፋጭ(Sweet Sorghum) ይባላሉ።

ሰብሉ በአፍሪካና በአሜሪካ በብዛት ይመረታል።ሰብሉን በብዛት የሚያመርቱ አገሮች ናይጄሪያ፣ሱዳን፣አሜሪካ፣ኢትዮጽያና ሕንድ ናቸው።በአፍሪካ ዓመታዊ የምርት መጠኑ 28ነጥብ 3ሚሊዮን ቶን  ይገመታል።

ናይጄሪያን በቀዳሚነት ያስቀመጠችው የአፍሪካ  አህጉር  ከዓለም 46 በመቶ አምራች ናት፤አሜሪካ 35 በመቶውን ድርሻ ትወስዳለች።

አሜሪካ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2024 ያመረተችው 61ነጥብ 3ሚሊዮን ቶን እንደነበር መረጃዎች አመላክተዋል።

በዓለም ደረጃ ሲታይ በማሽላ የሚለማው መሬት መቀነስ እየታየበት ሲሆን፣ምርታማነቱ ግን በተለይ ባደጉና ዘመናዊ የግብርና መንገዶችን ተጠቅመው በሚያለሙ አገሮች እየጨመረ መጥቷል።

በአውሮፓ በተለይም በሩሲያ፣ፈረንሳይና ጣልያን ሰብሉ  በስፋት በመልማት ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።  

ማሽላ ከበቆሎ ሦስት እጥፍ በሆነ ደረጃ ድርቅን የመቋቋም አቅም ያለው በመሆኑ ለአየር ንብረት ለውጥ የተሻለ እንደሚያደገው በሰብሉ ላይ የተደረጉ ጥናቶች አሳይተዋል።

በኢትዮጵያ ማሽላ ከበቆሎ፣ ከስንዴና ከጤፍ ቀጥሎ ለአገሪቱ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ጠቃሚ ሰብል ነው፡፡  

በዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታው ደግሞ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ 

በንጥረ ነገር ይዘቱ በካርቦሃይድሬት፣ በፕሮቲን፣ በቫይታሚንና በማዕድን የበለፀገ፤ ከኢኮኖሚ አንፃር ለምግብ፣ ለእንስሳት መኖ፣ ለግንባታ፣ ለማገዶና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል ነው፡፡ 

እንዲሁም በባህላዊና ማህበራዊ በኩልም የጎላ ፋይዳ አለው፡፡

ግብርና ሚኒስቴር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማሽላን አገራዊ ጠቀሜታ ግምት ውስጥ በማስገባት ማሽላ ከብሔራዊ ፕሮግራሞች አንዱ ሆኖ እንዲካተት አድርጓል፡፡ 

ሚኒስቴሩ ብሔራዊ አደረጃጀትን ዘርግቶ ከአላያንስ ፎር ግሪን ሪቮሉሽን አፍሪካ(AGRA) ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የማሽላ ፕሮግራም ሰነድ ሰሞኑን ከዘርፉ ከፍተኛ ተመራማሪዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ገምግሟል።

ሰነዱ ፀድቆ ወደ ሥራ ሲገባ ተደብቀው የቆዩ የማሽላ ፋይዳዎች በስኬት ጎልተው ይወጣሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡

ማሽላ ትኩረት ባልተሰጠው ጊዜ እንኳን፤በአገሪቱ  ከሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በመሸፈን 25 ሚሊዮን ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የገቢ ምንጭና የምግብ ዋስትና የሆነ ሰብል ነው፡፡ 

ብሔራዊ የማሽላ ፍላግሺፕ ፕሮግራም ከ2018 – 2022 የሚተገበር ሲሆን፣ በፕሮግራሙ ማጠናቀቂያ ዓመት ላይ ከምርቱ እመርታ እንደሚጠበቅ ሰነዱ አመላክቷል፡፡ 

አሁን  በሄክታር የሚመረተው በአማካይ 29 ኩንታል ምርት ወደ 50 ኩንታል ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል ይላል ሰነዱ።  

ከአግሮ ኢንዱስትሪ ጋርም ትስስር በመፍጠር ጠቀሜታው እያደገ እንደሚሄድ ማመላከቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያወሳል፡፡

እንዲሁም የኑሮ መሠረታቸውን በማሽላ ላይ ካደረጉ 25 ሚሊዮን  አርሶ አደሮች በተጨማሪ  የ2ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን የምግብ ዋስትና ያረጋግጣል። 

በሰብሉ በሚፈጠረው የሥራ ዕድልና ምርታማነት 1 ነጥብ 7 ሚለዮን ሰዎችን ከድህነት የሚያወጣና የግብርናው ዘርፍ ለአገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን ድርሻ በአምስት በመቶ ያሳድጋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

የማሽላ ምርጥ ዘርን ለማሻሻል በአግባቡ ከተሰራ ድርቅና አደጋን ከመቋቋም አቅሙ ጋር ተዳምሮ በምርታማነት አንደኛ ደረጃ ከያዘው በቆሎ መብለጡ አይቀርም የሚል የባለሙያዎች ግምትም አለ።



ኢኮኖሚማሽላግብርና

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!