እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
05:13:30 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ምርጫ 2018

ሲቪል ማህበራት በምርጫው ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ተጠየቁ

2 ደቂቃ ንባብ
ሲቪል ማህበራት በምርጫው ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ተጠየቁ

በአገሪቱ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ይካሄዳል።በምርጫው ለመወዳደር የተዘጋጁ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳና የምርጫ  ክርክሮች በማድረግ የመራጮችን ቀልብ ለመሳብ በመሞከር ላይ ናቸው።

ለምርጫው እስካለፈው ሣምንት ድረስ 37 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ድምፅ ለመሰጠት ተመዝግበዋል።የመራጮች ምዝገባም እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ተራዝሟል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫው ከሚሳተፉ ፓርቲዎች ጋር በዚህ ሣምንት በተለይም በሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል።

ቦርዱ በክልሎች ባሰማራቸው በጎ ፈቃደኞች አማካይነት ለመራጮች ትምህርት መሰጠቱንም አስታውቋል።

ቦርዱ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙኃን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ከሚያደርጉት ክርክሮች በተጨማሪ፤በራሱ ያዘጋጀውን ክርክር  ማካሄዱም ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እያለ ሲቪል ማህበራት ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ  ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ጠይቋቸዋል።

‌የምክር ቤቱ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ባለሥልጣንን የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።

‎በመድረኩ በሲቪል ማኅበራት አሠራር፣ የማህበራት ምዝገባ ሒደት፣ በጎ ፈቃደኝነት፣ የማህበራት ገንዘብ አጠቃቀምና በምርጫ ዝግጅት ዙሪያ ያተኮረ ሪፖርት ቀርቧል።

‎የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግሥቱ እንዳሳሰቡት በአገሪቱ የሚደራጁ የሲቪል ማኅበራት ከቁጥር ባለፈ፤ በጥራትና በይዘት ኢትዮጵያን የሚመጥኑ እንዲሆኑ በትኩረት  መሥራት ያስፈልጋል።

ማኅበራቱ ሲቋቋሙ ካለሙት ዓላማ አንጻር ውጤታማ  መሆናቸውን ለማረጋገጥ የማያቋርጥ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ፣ ከተለያዩ ምንጮች የሚሰበስቡት ገንዘብ ለታለመለት ተግባር ብቻ መዋሉን በቁጥጥር ሥራ ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

‎የሲቪል ማኅበራት በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ እንዲሆን ሚናቸው የላቀ በመሆኑ በምርጫ ዙሪያ የሚሰሩ ማኅበራትን አቅም ለማብቃት ጥረቱ እንዲጠናከር አሳስበዋል።

ማኅበራቱ በማንኛውም ወገን ተጽዕኖ ሥር ሳይወድቁ ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግም ሰብሳቢዋ አስገንዝበዋል።

‎የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ እንዳመለከቱት የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያደርጉት ጥረት ከመንግሥት የልማት ዕቅድ ጋር ተቀናጅቶ መካሄድ አለበት።

ባለሥልጣኑ ማኅበራቱ የሚያከናውኗቸው ተግባራት ከአገሪቱ የልማት ግቦች ጋር የተቆራኚና ሕዝብን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በየደረጃው ያለውን የቁጥጥርና የክትትል ሥራ በመስክ ምልከታ ጭምር ታግዞ እንዲያከናውን አስገንዝበዋል።

‎ዜጎች የመደራጀት ሕገ-መንግሥታዊ መብት ያላቸው መሆኑን የገለጹት ምክትል ሰብሳቢው፣ ምዝገባ በሚከናወንበት ወቅት ከአገር ደህንነትና ሰላም አንጻር የሚነሱ ጉዳዮችን ከሚመለከታቸው የጸጥታና ደህንነት አካላት ጋር በቅንጅት በማጣራት እንዲከናወን ጠቁመዋል።

ማኅበራቱ ለታለመላቸው በጎ ዓላማ ብቻ መቆማቸውን ለማረጋገጥ ፣ ምዝገባው ጥንቃቄ የተሞላበትና በቅንጅታዊ አሠራር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ምክትል ሰብሳቢው አመላክተዋል ።

‎የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ መጪው አገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በምርጫ ዙሪያ የሚሰሩ ማኅበራት ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በምርጫው ሂደት ላይ የሚሳተፉ የሲቪል ማኅበራት አገራዊ ኃላፊነታቸውን በመረዳት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውጤታማ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

‎ይህንን እውን ለማድረግ ማኅበራቱን በማብቃትና በመደገፍ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ዕቅዱ ማኅበራቱ ከአድሎአዊ አሠራር በጸዳ መልኩ ለዜጎች ግንዛቤ በመፍጠርና የምርጫ ሂደቱን በመታዘብ ረገድ ውጤታማ እንዲሆኑ ያለመ መሆኑ ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ ማኅበራቱ  ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ክትትልና ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፣ የምርጫውን ሂደት ተዓማኒነት ለማረጋገጥ  የነፃ ስልክ መሥመር አገልግሎት መዘርጋቱንም አስታውቀዋል።



ምርጫሲቪል ማህበራትየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትምርጫ 2018

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!