እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
05:14:57 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ማህበራዊ

ስልጠናው የወጣቱን የዲጂታል ክህሎት አሳድጓል

2 ደቂቃ ንባብ
ስልጠናው የወጣቱን የዲጂታል ክህሎት አሳድጓል
በኢትዮጵያ የዲጂታል ክህሎት አቅምን በማሳደግ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያለመ ስልጠና በመላው የአገሪቱ ክፍሎች በመሰጠት ላይ ነው።

ኢትዮጵያ ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ለመድረስና ወጣቶቿን የቴክኖሎጂወ ተቋዳሽ ለማድረግ የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሆነች ይታወቃል።

ስልጠናው ወጣቶች ከቴክኖሎጂ አድናቂነትና ተመልካችነት ወጥተው፤ቴክኖሎጂውን ፈጣሪና አቅራቢ የሚሆኑበትን አቅም ለመፍጠር እንደሚያስችላቸውም ይታመናል።

መንግሥት በኢትዮጵያ የዲጂታል ክህሎት አቅምን በማሳደግ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያለመ ስልጠና በመላው የአገሪቱ ክፍሎች በመስጠት ላይ ነው።

 ከዚህም የጂንካ ከተማ  ሰልጣኞች የኢትዮ  ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ክህሎታቸውን ማሳደጉን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በከተማው ስልጠናውን የተከታተሉ ሰልጣኞችም የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከቴክኖሎጂ ጋር በቀላሉ ለመለማመድ አስችሎናል ብለዋል።

የከተማዋ ነዋሪ ወጣት በረከት ዓባይነህ በኢትዮጵያ ኮደርስ ስልጠና ከተካተቱ አራት ኮርሶች ሙሉውን በማጠናቀቅ ሰርተፊኬት መውሰዱን ገልጿል።

በመረጃ ትንተና፣ በአንድሮይድ፣ በፕሮግራሚንግና በሰው ሰራሽ አስተውሎት የስልጠና መስኮች በቂ ዕውቀት ማግኘቱን ተናግሯል።

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከቴክኖሎጂ ጋር በቀላሉ እንዲላመዱ እንዳገዛቸው የገለጸችው ደግሞ ወጣት ምህረት ፍሬው ናት።

ከፕሮግራሚንግ በቀር ሦስት ኮርሶችን በማጠናቀቅ ሰርተፊኬት መውሰዷን የምትናገረው የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የወጣቱን የዲጂታል ክህሎት የሚያሳድግ ጠቃሚና አቅም ገንቢ መሆኑን ተናግራለች።

ስልጠና በሰው ሰራሸ አስተውሎት ዓለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ከፍታ ለመረዳት ያስችላል ያለው ደግሞ ወጣት በቃሀኝ ጥላሁን ነው።

በወሰዳቸው የፕሮግራሚንግና የዳታ አናሊስስ ስልጠናዎች ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚያስችለውን የዲጂታል ዕውቀት ማሳደጉን በመግለጽ።

መንግሥት እንዲህ አይነት ጠቃሚ ስልጠናዎችን በነፃ በመስጠት ወጣቱን ብቁና ተወዳዳሪ ለማድረግ የጀመረውን ጥረትም ይበል የሚያሰኝ ነው ብሎታል።

የጂንካ ከተማ አስተዳደር ሳይንስና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ዩኒት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ግርማ እንዳሉት በከተማ አስተዳደሩ ዘንድሮ ከ4 ሺህ በላይ ወጣቶች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወስደዋል።

በስልጠናው ከተሳተፉት ውስጥ ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑት ስልጠናቸውን ሙሉ ለሙሉ አጠናቀው ሰርተፊኬት መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።



ወጣቶች

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!