እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:51:54 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ

በኢትዮጵያ የተገነባው ጎተራ ክላውድ (G-Cloud)

2 ደቂቃ ንባብ
በኢትዮጵያ የተገነባው ጎተራ ክላውድ (G-Cloud)
ጎተራ ክላውድ ፈጣን፣ የተቀናጀና ውጤታማ የዲጂታል አገልግሎት አቅርቦትን በማስቻል የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና የመረጃ በላይነት የሚያረጋግጥ አገራዊ ሀብት ነው።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ጎተራ ክላውድ (G-Cloud)የተሰኘ የዲጂታል ሉዓላዊነትና የመረጃ በላይነት ማረጋገጫ መሠረተ ልማት መገንባቱን አስታወቀ።

ተቋሙ ይህንን አሰመልክቶ ባወጣው  መግለጫ እንዳመለከተው
የዘመኑ ትልቁ ሀብት እና ኃይል "መረጃ" (Data) ነው።
መረጃን መቆጣጠር ደግሞ አገራዊ ሉዓላዊነትን የማስጠበቅ ያህል ከፍተኛ ትርጉም አለው ይላል።

በዚህም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) በራሱ አቅም የገነባው የ“ጎተራ ክላውድ - G-Cloud” መሠረተ ልማት የአገሪቱ መረጃ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ በአገር ውስጥ ለማከማቸትና ለማስተዳደር የተቋቋመ የቴክኖሎጂ ምሽግ መፍጠሩን ገልጿል።

"የኢትዮጵያ የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ስኬታማ እንዲሆን አስተማማኝ የዲጂታል መሰረተ ልማት የግድ ይላል" ያለው  መግለጫው፣ጎተራ ክላውድ የኢ-መንግሥት (e-Government) ፣ የዲጂታል ፋይናንስና ሌሎች ዘርፎች አገልግሎቶቻቸውን በዘመናዊና ፈጣን ቴክኖሎጂ ለዜጎች እንዲያቀርቡ በማድረግ ቁልፍ ሞተር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ብሏል።

የአውሮፓ ኅብረት፣ ቻይናና ሌሎችም በቴክኖሎጂ ያደጉ አገሮች የዜጎቻቸውንና የተቋማትን ምስጢራዊ መረጃዎች በውጭ አገር ሰርቨሮች ላይ ማከማቸትን ይከለክላሉ በማለትም በዘርፉ ያለውን ዓለም አቀፍ ልምድም አጋርቷል።

አስተዳደሩ "መረጃን በሀገር ውስጥ ማከማቸት" የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ተደርጎ እንደሚወሰድም አጽንኦት በመስጠት አብራርቷል። 

በአስተዳደሩ የተገነባው ጎተራ ክላውድ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የደህንነት ስታንዳርድ እንድትተገብርና መረጃዎቿን በራሷ ለመቆጣጠር አቅም ፈጥሮላታል በማለትም ጠቀሜታውን አመልክቷል።

ጎተራ ክላውድ ፈጣን፣ የተቀናጀና ውጤታማ የዲጂታል አገልግሎት አቅርቦትን በማስቻል የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና የመረጃ በላይነት የሚያረጋግጥ አገራዊ ሀብት ነው ሲልም ገልጾታል።

ጎተራ ክላውድ የክላውድ አገልግሎት በኮምፒዪተር፣ ስቶሬጅ፣ ኔትወርክና ሶፍትዌሮችን በኢንተርኔት ለማግኘት የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ነው።

በከፍተኛ የደህንነት መርሆዎችም የመሠረተ ልማት፣ የፕላትፎርም፣የሶፍትዌር፣የመረጃ ክምችትና መልሶ ማግኛ አገልግሎቶች እንደሚሰጥ የአስተዳደሩ መግለጫ ያሳያል።

የአገር ውስጥ የክላውድ አገልግሎት ሦስት ዓበይት ጥቅሞች እንዳሉት መግለጫው አስረድቷል።አንደኛው ተቋማት የራሳቸውን ውድ የሆነ ዳታ ማዕከል (Data Center) ለመገንባት የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጪና የውጭ ምንዛሪ ያስቀራል።

ሁለተኛው ከውጭ የቴክኖሎጂ ጥገኝነትን በመቀነስ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ነፃነትን  ማረጋገጥ መሆኑን አመልክቷል።

ሦሰተኛው ጥቅሙ ደግም የመረጃ ደህንነትን ከማንኛውም የውጭ ጥቃትና የመረጃ ስርቆት በከፍተኛ ደረጃ  መጠበቅ ነው ብሏል።








ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንሳይንስና ቴክኖሎጂጎተራ ክላውድ

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!