
ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ከቡና ለማግኘት ያሰበችውን ገቢ ለማሳካት ምርቱን በፍጥነትና በብዛት ለማዕከላዊ ገበያ እንዲቀርብ ግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ።
አገሪቱ በበጀት ዓመቱ 600 ሺህ ቶን ቡና በመላክ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዳለች።
ቡና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለይም በግብርናው ዘርፍ ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ቡና ከአገሪቱ አጠቃላይ የግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ ገቢ ውስጥ ከ50 እስከ 65 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ሲያበረክት ቆይቷል።
የቡናን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተደረገው ጥረትና የምርቱ የዓለም አቀፍ ፍላጎት መጨመር ለዚሁ አዎንታዊ አዝማሚያ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ኢትዮጵያ ከብራዚል፣ ቪዬትናምና ከኮሎምቢያ በመቀጠል በዓለም አቀፍ ደረጃ አራተኛዋ ከፍተኛ የቡና ላኪ ለመሆን መብቃቷን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የሚኒስቴሩ የሕዝበ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ይመር ዳውድ የቡና ዓለም አቀፍ ገበያ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ 600 ሺህ ቶን ቡና በመላክ 3ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት እየተሰራ ሲሆን፣በበጀት ዓመቱ የስድስት ወራት አፈጻጸም የወጪ ንግድ ዕቅድ የተያዘለትን ግብ በኤክስፖርት መጠን ለማሳካት ተግዳሮት ገጥመውት እንደነበር አውስተዋል።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት 200ሺህቶን በመላክ 1 ነጥብ 35 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
አፈጻጸሙ ከገቢ አኳያ ሲታይ ከዕቅዱ በላይ አፈጻጸም ታይቶበታል፡፡ ሆኖም ከመጠን አኳያ ለማቅረብ ከታቀደው 74 በመቶ ብቻ ነው ያተሳካው ብለዋል።
ለዚህመ ዋነኛው ምክንያት ምርት ማከማቸት እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ተመን ይጨምራል የሚል የተሳሳተ ግምት ተጠቃሽ መሆኑን አመላክተዋል።
አቅርቦቱን ለማሳካትና እያሽቆለቆለ ከመጣው የዋጋ ውድቀት ለመታደግ በእጅ ያለውን ፈጥኖ ለዓለም ገበያ ማቅረብ፣ ምርቱ እንዳይሸሸግ ግንዛቤ መፍጠርና ምርት በሚሸሽጉ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል ሥራ አስፈጻሚው።
አርሶ አደሮች ለተሳሳተ የገበያ መረጃ ተጋላጭ በመሆናቸው፤ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ የኅብረት ሥራ ማህበራት፣ የክልል ባለድርሻ አካላት እንዲሁም መገናኛ ብዙኃን በቅንጅት የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ እንዲደረግ ጠቁመዋል።
የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የቡና ግብይት ግብረ-ኃይሉን ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በማቀናጀት እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በመውረድ አስፈላጊውን ክትትል ማድረግና ሕግ በማስከበር ሂደቱን እንዲያጠናክር ሥራ አስፈጻሚው ጠይቀዋል።
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!