
በዚህ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ‘ሆሣዕና በአርያም’’ ‘ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት’’ ‘ዕለተ ሆሣዕናሁ አርአየ… ‘ ወዘተ. በማለት ሆሣዕና የሚለውን ቃል ቅዱስ ያሬድና ሌሎችም አባቶች በየቦታው እየጠቀሱና እየተዘመረለት በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ እየተረከ ስለሚዘምር በጌትነትና በክብር በውዳሴና ቅዳሴ ሆሣዕና በአርአያም እየተባለ በሽማግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮችም ልሳን ሳይቀር እየተመሰገነ ወደ ኢየሩሳሌም በከብር ሲገባ ለሰጣቸው ለተቀደሰ ሰላሙና ፍቅሩ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ ነው።
የሆሣዕና በዓል በቤተክርስቲያን ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ ሕዝቡ ፀበርት ወይም ዘንባባ በመያዝ ‘ቡርክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር – በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረክ ነው።’’ መዝ.117፣26 በማለት ስለተቀበሉት ይህን በማሰብና በማድረግ ቤተክርስቲያናችን ዘንባባ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ታድላለች። በቤተክርስቲያን በአራቱም ማዕዘናት ይህን በዓል የሚመለከቱ የቅዱስ ማቴዎስ (ማቴ. 21፣1-17)፤ የቅዱስ ማርቆስ፣(ማር.11፣1-10)፤ የቅዱስ ሉቃስና (ሉቃ.19፣29-38)፤ የቅዱስ ዮሐንስ (ዮሐ.12፣12-15) ወንጌላት ይነበባሉ ።
ሰሙነ ሕማማትና ሰቅለት
ሰሙነ ሕማማት ተብሎ የሚጠራው ወቅት ከዐቢይ ጾም መጨረሻ ከሆሣዕና ዋዜማ ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ባሉት ቀናት ውስጥ ያለው ሳምንት ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ይህንን ወቅት አስመልክቶ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ‹‹ውእቱ ነሥአ ደዌነ ወጾረ ሕማመነ፤ እርሱ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፤›› በማለት የነገረ ሕማማቱን ምሥጢር አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ በዚህም መሠረት በኋለኛው ዘመን እግዚአብሔር ወልድ ስለኛ ስለ ሰው ልጆች ድኅነት ሲል ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋም ነፍስ ነሥቶ በፈቃዱ ሰው ሆኖ በፈቃዱ መከራ መስቀልን ተቀበለ፡፡ በመስቀሉም ላይ ሳለ በፈቃዱ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ፡፡
በዚህ ሳምንት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ በሙሉ ያደረገውን ትድግና ቅዱሳት መጻሕፍት በተለይም ግብረ ሕማማት የተባለው ነገረ ሕማማቱን መከራውና መሰቀሉን በሰፊው ይነገርበታል።
የስቅለት (crucifixion) ቀን እጅግ ልዩ ናት፡፡ የስቅለት ዕለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ “የድኅነት ቀን” ወይም ‹‹መልካም ዓርብ›› ይባላል፡፡ ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡ ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት (ማቴ. 27፥1-57)፡፡ ይህን አጥተቀል የሚሉት ነገር ሳይኖራቸው ጌታችንን ለፍርድ ያቀረቡት አይሁድ ጲላጦስ እነርሱ ወደ ተሰባሰቡበት ቦታ ወጥቶ ‹‹ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደል ምንድን ነው?›› ሲል በጠየቃቸው ጊዜ በቂ ምላሽ አላቀረቡም፡፡
በግብረ ሕማማት‹‹የማይሞት መለኮት ስለ እኛ የሞትን ጽዋ ተቀብሎ በሰውነቱ ሞተ! ወዮ ለዚህ አንክሮ ይገባል፡፡›› እንደተባለ ስለኛ በፈቃዱ ይሞት ዘንድ ፈቃዱ ነበርና በአይሁድ ጭካኔ ምክንያትነት ሞት ተፈረደበት፡፡
ቀዳም ስዑር
በሰሙነ ሕማማት በስቀለት ማግስት የሚውለው ቅዳሜ ቀዳም ሥዑር በመባል ይጠራል፡፡ በዚህ ዕለት ከድሮው በተለየ መልኩ ጌታችን መድኂታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምና ልጆቹን ከዲያብሎስ አገዛዝና እስራት ነጻ ለማውጣት የተቀበለውን መከራ፣ እንዲሁም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ማደሩን በማሰብ በጾም ታስቦ ስለሚውል ቀዳም ስዑር ወይም የተሻረው ቅዳሜ ተብሏል፡፡ የማይጾመው ቅዳሜ ስለሚጾም ስዑር /የተሻረ/ ተብሏል፡፡
የቀዳም ስዑር ሌሎች ስያሜዎች ለምለም ቅዳሜና ቅዱስ ቅዳሜ ይባላሉ።
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!