እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
08:29:14 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ኢኮኖሚ

አዲስ አበባን ናፋቂው የዘርፍ ጉባዔ

2 ደቂቃ ንባብ
አዲስ አበባን ናፋቂው የዘርፍ ጉባዔ
አየር መንገዱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2023 ያስተናገደውን ጉባዔ ዳግም እንዲያስተናግድ ዕድል ተሰጠው፤ዕድሉን ተጠቅሞ እንግዶቹን ለማስተናገድ ሽር ጉዱን ተያይዞታል፡፡
አዲስ አበባ ከሦስት ዓመታት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ አስተናግዳዋለች፣ዘንድሮም በደንብ ተዘጋጅተሽ ጠብቂኝ እንጂ፤ አክራሞታች ከአንቺ ጋር ነው ተብላለች፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ በጣም ውጤታማና ስኬታማ ከሚባሉ አየር መንገዶች አንዱ ነው፡፡

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2023 ያስተናገደውን ጉባዔ ዳግም እንዲያስተናግድ ዕድል ተሰጠው፤ዕድሉን ተጠቅሞ እንግዶቹን ለማስተናገድ ሽር ጉዱን ተያይዞታል፡፡

አየር መንገዱ እንዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጉባዔውን ዳግም ለማስተናገድ የተሰጠው በውጤታማነቱ መሆኑንም ጉባዔውን የጠራው አካል ገልጿል፡፡

አየር መንገዱ የአህጉሪቱን አቪየሽን ዘርፍ በማሳደግ ሚናውን እየተጫወተ ነው፡፡በተለይም አፍሪካን ከአውሮፓ፣ከእስያና ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር በማገናኘት የሚጫወተው ሚና ወደር እንደሌለው ብዙዎች ይመሰክሩለታል፡፡

እሺ አዲሰስ አበባስ ካላችሁ፤መልሱ‹‹ከተማዋ ባላት ስትራጂያዊ አቀማመጥና ጠንካራ የአፍሪካ አቪየሽን መሠረተ ልማት በአህገሪቱ አቪየሽን ዘርፍ ለመወያየት ምቹ ናት፡፡››

የኢትዮጵያ አየር መንገድና አዲስ አበባ የተመረጡት የአፍሪካ አቪየሽን ዘርፍ መሪዎች ዓመታዊ ጉባዔ እንዲያስተናገዱ ነው፡፡

የዓለም አቀፍ አየር ትራንስፖርት ማህበር የአፍሪካ ቅርንጫፍ እንደገለጸው፤የዘርፉ መሪዎች 2026 ዓመታዊ ስብሰባቸውን በግንቦት ወር መጀመሪያ በከተማዋ ለማድረግ ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

ጉባዔው በአህጉሪቱ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ልማት ላይ አትኩሮ ለሁለት ቀናት የሚወያይ ሲሆን፣ፖሊሲ አውጪዎች፣የአየር መንገዶች መሪዎች፣የዘርፉ ተቆጣጣሪዎችና የአቪየሸን ዘርፍ ባለሙያዎችም ይሳተፉበታል፡፡

ጉባዔው ‹‹በአፍሪካ የአቪየሽን ዕድገት፣ግንኙትንና ውጤታማነትን ማሳደግ›› በሚል መሪ ቃል ለሁለት ቀናት ይክሄዳል፡፡

በዚህም ዘርፉ የአህጉሪቱን ኢኮኖሚዊና ማህበራዊ ዕድገት በማፋጠን በሚጫወተው ሚና ትኩረት የሚያደርግ  ሲሆን፣ የአቪየሽን ዘርፍ  ካሉበት ችግሮች በማላቀቅ ዘላቂ ዕድገት የሚያመጣበት አቅጣጫ የሚተልም ፍኖተ ካርታ ያዘጋጃል፡፡

አፍሪካ ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡና የኢኮኖሚ መሠረታቸውን ከሚያሰፉት አህጉሮች አንዷ  ብትሆንም፤የአቪየሽን ኢንዱስትሪዋ በዓለም ያለው ድርሻ አነስተኛ ነው፡፡የዘርፉ ባለሙያዎች የበራራ መሥመሮች፣ ቱሪዝምንና ድንበር ዘለል ንግድን  የምታስፋፋባቸው ዕድሎች ሰፊ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

የተበታተነና ያልተዋሃደ የቁጥጥር ሥርዓት መኖር፣ የመሠረተ ልማት  ተቋማት ውሱነንትና ዘርፉን ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልገው ወጪ መናር የዘርፉን ዕድገት ማነቆዎች መሆናቸውን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በአዲስ አበባ የሚካሄደው ጉባዔ ባለድርሻ አካላትን በአንድ በማሳባሰብ ለችግሮቹ መፍትሄዎች ያመላክታል የሚል ተስፋም ተጥሎበታል ይላል የማህበሩ መግለጫ፡፡

የማህበሩ የአፍሪካና መካከኛው ምሥራቅ ክፍል ምክትል ፕሬዚዳንት ካሚል አላዋድሂ በሰጡት አስተያየት የአህጉሪቱ የመሠረተ ልማት ችገሮች ከተቃለሉ፤የአቪየሽን ዘርፍ ሚና እያደገ ይሄዳል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ይህም የበረራ ደህንነት ደረጃዎችን በማሻሻል፣ የአቪየሽን መመሪያዎች ሁሉም አገሮች እንዲጠቀሙባቸው አድርጎ በማዘጋጀትና የአስተዳደር ወጪዎች በመቀነስ ይመጣል ብለው ያምናሉ፡፡

በዘርፉ የሚመራው ኃይል የአመራርና የሠራተኞችንም ብቃት በማሳደግ ሊመጣ ይችላል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ የተደረገ ትንበያ እንደሚያመለክተው፤የአፍሪካ አቪየሽን ፍላጎት በየዓመቱ ከሦስት እስከ አራት በመቶ ያድጋል፡፡ይህን ፍላጎት ለማሟላት በፍጥነትና በጥንካሬ መሰራት አለበትም ምክራቸው ነው፡፡ 

በጉባዔው የአህጉሪቱ መንግሥታት መሪዎች፣ከአህጉሪቱና ከአህጉሪቱ ውጭ የሚገኙ የአየር መንገዶችና የአቪየሽን ድርጅቶች  ኃላፊዎች ንግግር  ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ለጉባዔው የወጣው መርሐ ግብር ያመለክታል፡፡

እንዲህ ነው መመረጥ!!! ውጤትና ስኬት ከመልካም መስተንግዶ ጋር ሲጣመሩ፤መልካም ገጽታንና ኢኮኖሚንም ይገነባሉ፡፡


ጉባዔየኢትዮጵያ አየር መንገድአቪዬሽን

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!