
በአዲስ አበባ በቀጣዩ ወር ዓለም አቀፍ የከተማ ተራራ ላይ የቢስክሌት ውድድር እንደምታስተናግድ የኢትዮጵያ ቢስክሌት ፌዴሬሽን ገለጸ።
"ሲቲ ማውንቴን ባይክ ኤሊሚኔተር ፕሮ ሊግ" የሚል ስያሜ የተሰጠው ውድድር ዓለም አቀፉ የቢስክሌት ኅብረት (UCI) የውድድር መርሃ ግብር ውስጥ የተካተተና እውቅና ያለው ነው።
በአፍሪካ የመጀመሪያ የሚሆነው ውድድር ሚያዝያ 25 ቀን 2018 በፒያሳ አድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ዙሪያ ይካሄዳል።
ውድድሩ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት ዋናው ውድድር መሆኑንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
በውድድሩ ከ24 የአውሮፓና ከ10 የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ከ60 እስከ 80 የሚደርሱ ምርጥ ቢስክሌተኞች እንደሚሳተፉም ተገልጿል።
ኢትዮጵያውያን ቢስክሌተኞች የውድድሩ ተሳታፊ ይሆናሉ።
ይህም ኢትዮጵያን በዓመታዊው የዓለም አቀፍ የከተማ ማውንቴንባይክ ካሌንደር ውስጥ ከባርሴሎና በመቀጠል ሁለተኛዋ መዳረሻ ያደርጋታል።
የኤሊት ተወዳዳሪዎች (ወንድ እና ሴት) የጊዜ ሙከራ፣ የግማሽ ፍጻሜና የፍጻሜ ውድድሮች ይከናወናሉ።
ውድድሩን ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቀጥታ የሚተላለፍ ሲሆን፣ ከ20 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች ይከታተሉታል ተብሎ ይጠበቃል ይላል የኢዜአ ዘገባ።
ከዋናው ውድድር አስቀድሞ ሚያዝያ 24 ቀን 2018 ለሁሉም ክፍት የሆነ ውድድር የሚካሄድ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን ቢስክሌተኞች የመሳተፍ እድል ያገኛሉ።
በዕለቱ የአማተር ቢስክሌተኞች፣ የልጆችና የሰዓት ሙከራ ውድድሮች ይካሄዳሉ።
ፌዴሬሽኑ ባወጣው መረጃ ቀጣዩ ወር የሚስተናገደው ዓለም አቀፍ ውድድር ለኢትዮጵያ ስፖርት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት ።
ውድድሩ ኢትዮጵያን ለዓለም ከማስተዋወቅ ባሻገር፣ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸውን ውድድሮች የማዘጋጀት አቅም እንዳላት በተግባር እንደሚያሳይ አመልክቷል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች በሀገራቸው ከዓለም ኮከቦች ጋር የመወዳደር እድል እንዲያገኙና ወደ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ የሚሸጋገርበት ድልድይ እንደሚሆነ ነው ፌዴሬሽኑ የገለጸው።
ለኢትዮጵያ የስፖርት ቱሪዝም እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎም ይታመናል።
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!