
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በአገልግሎቱ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ እንደተናገሩት ኩባንያው የአገሪቱን ዲጂታል ሽግግር እውን የሚያደርጉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት በመዘርጋት ላይ ነው።
ቴሌሳይን የተሰኘው ዲጂታል ሶሉሽን በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑንም ገልጸዋል።
አዲሱ ቴክኖሎጂ አስተማማኝ የዲጂታል ማንነት ማረጋገጥንና ሕጋዊ ተቀባይነት ያለውን የዲጂታል ፊርማ ሥርዓትን ወደ ሥራ እንደሚያስገባ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አብራርተዋል።
በዚህም የመንግሥት አሰራሮችን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል በመቀየር ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል።
ቢሮክራሲን በመቀነስ፣የአገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግና አገራዊ የዲጂታል ተጠቃሚነትን በማስፈን ረገድ የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረውም አስረድተዋል።
የዲጂታል አገልግሎት መስጫው ዜጎች ያለ ምንም መልክዓ-ምድራዊ ገደብ የመንግሥት አገልግሎቶችን በኦንላይን እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
ይህም አገሪቱ ወደ ሙሉ ዲጂታል መንግሥት (E-Government) የምታደርገውን ሽግግር በየሚያፋጥን ሲሆን፤ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች አገልግሎቶችን በፍጥነት፣ በብቃትና በታማኝነት ለማግኘት ያስችላቸዋል ብለዋል።
ኩባንያው መሰል ዘመናዊ የዲጂታል መፍትሔዎችን በማቅረብ፣ሀገራዊ የዲጂታል ጉዞን የመደገፍና የማብቃት ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፤ ሚኒስቴሩ የተጣለበትን ተልዕኮ በላቀ ብቃት ለመወጣት የሚያስችለውን ተቋማዊ ለውጥ እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ ሲሆን፥የዲጂታል አገልግሎት መጀመሩም ለውጥ እንደሚያመጣ ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመቀናጀት የቴሌሳይን (teleSign) እና ዲጂታል ሞፋ (Digital MoFA) የተሰኙ ቴክኖሎጂ መር አገልግሎትን በይፋ መጀመሩን አስታውቀዋል።
የዲጂታል ሥርዓቶቹ ከየትኛውም ቦታ ሆነው ዘመናዊ አገልግሎት ለማግኘት ሲናፍቁ ለነበሩ የዲያስፖራ አካላትና መላው ዜጎች የምሥራች ናቸው ብለዋል።
በተጨማሪም ሕጋዊ ተቀባይነት ያለውና የሰነዶችን ኦሪጅናልነት የሚያረጋግጥ የዲጂታል ፊርማ ሥርዓትን ሥራ ላይ ማዋል ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
አገልግሎቱን ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ጋር በማስተሳሰር፣ የተገልጋይ ማንነት ማረጋገጫ ሥርዓት መዘርጋቱንም ጠቅሰዋል።
ዲጂታል አገልግሎቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣በሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ አገልግሎትና በፍትህ ሚኒስቴር መካከል የተቀናጀ የመረጃ ፍሰት እንደሚፈጥርም አምባሳደር ብርሃኑ አንስተዋል።
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!