እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
08:28:15 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ማህበራዊ

ኢድ አል ፈጥርና ረመዳን ምንና ምን ናቸው?

6 ደቂቃ ንባብ
ኢድ አል ፈጥርና ረመዳን ምንና ምን ናቸው?
የጾም ፍቺ ከአራቱም ማዕዘናት ሙስሊሞች አደባባይ በመገኘት የጾም ፍቺ ስግደት በጋራ ይፈጽማሉ።
1 / 3

በኢድ አል ፈጥር በዓል ሰዎች የመልካም ምኞት መግለጫዎቻቸውን በተለያየ መልኩ የሚገልጹ ሲሆን፤ በብዛት በጥቅም ላይ ከሚውሉት የመልካም ምኞት መግለጫዎች ውስጥ ግን "ኢድ ሙባረክ" (የተባረከ ኢድ) ወይም "ኢድ ሰኢድ" (መልካም ኢድ) የሚሉት ተወዳጅና በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉት ናቸው።

በመላወ ዓለም ለምትገኙ የእስልምና እምነት ተከታች ኢድ ሙባረክ!!!በማለት ጽሁፋችንን ጀምረናል፡፡

ቀኑ የበዓል ቢሆንም፤ የበዓሉ መነሻ በሆነው የረመዳን ወር ምንነትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እናወጋለን፡፡

‹‹ረመዳን›› የዓረብኛ ቃል ሲሆን በሂጅራ አቆጣጠር የዘጠነኛው ወር ስም መጠሪያ ነው። የረመዳን ወር ቅዱስ ቁርዓን ለሰው ልጆች ሁሉ ይደርስ ዘንድ ለነብዩ መሐመድ መውረድ የጀመረበት በመሆኑ ምንዳዋ ከሺሕ ወር በላይ እንደሆነ ይታመናል።

‹‹ጾም›› የሚለው ቃል በእስልምና ‹‹ማቆም›› ወይም ‹‹መከልከል›› የሚል ፍቺ አለው። በሸሪኣዊ አገባቡ ደግሞ ለአላህ ትእዛዝ ለመገዛት በሚል ውስጣዊ ውሳኔ ከፈጅር እስከ ጸሐይ ግባት ከምግብ፣ ከመጠጥና እኩይ ቃል ከመናገርና እኩይ ድርጊት ከመፈጸም መታቀብ የሚል ጥቅል ትርጉም እንዳለው መሐመድ ዓሊ (ዶ/ር) ‹‹ጾምና የጾም ፍቺ ማህበረ ባህላዊ ፋይዳ በእስልምና›› በሚል ባዘጋጁት ጽሁፍ አስፍረዋል።

በእስልምና ጾም በሁለት ይከፈላል፤በመደበኛ ጾምና በሱና ጾም ይከፈላል። የሱና ጾም በተለያዩ ምክንያቶችና ሁኔታዎች አብዛኛውን ጊዜ በግል የሚፈጸም ግዴታ የሌለበት የጾም አይነት ነው፡፡የሱና ጾም በማንኛውም ጊዜ ሊጾም ይቻላል። መደበኛው ጾም ደግሞ በጊዜ ገደብ ውስጥ በቡድን የሚጾም ግዴታ የሆነ የጾም አይነት ነው። ይህ የግዴታ ወይም መደበኛ ጾም በረመዳን ወር ይጾማል።

የሂጅራ የጊዜ አቆጣጠር በጨረቃ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የረመዳን ወር 29  ወይም 30 ቀናት ስለሚሆን ጾሙም በቀናቱ ርዝማኔ ይወሰናል። ረመዳን በሂጅራ አቆጣጠር ዘጠነኛው ወር የሚካሄድ የጾምና ጸሎት ወር ነው ፡፡ ረመዳን ከአምስቱ የእስልምና ማዐዘናት ውስጥ አንዱ ነው ። ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ ምትጠልቅ ድረስ ለአቅመ አዳም/ሔዋን በደረሱ የእምነቱ ተከታዮች ይጾማሉ፡፡

ጾሙ በተወሰኑ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ከተሞች በቀን እስከ 18 ሰዓታት ያህል ይጾማል፡፡ምክንያቱም በግሪንላንድ፣ ፊንላንድ፣ ሰኮትላንድ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ ፣ጣልያን፣ስዊዘርላንድናና ስፔን ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ከተሞች ፀሐይ ቶሎ ስለማትገባ ነው፡፡

የረመዳን ወር ጾም እድሜው ለደረሰና ጤነኛ ለሆነ ሙስሊም ሁሉ ግዴታ በመሆኑ አሳማኝ ምክንያቶች  የሌላቸው አማኞች በሙሉ እንዲጾመው ይገደዳሉ፡፡፡ለጾሙ የማይገደዱት በበሽታና በጉዞ፣ ነፍሰ ጡሮችና ልጅ የሚያጠቡ ናቸው፡፡  

በወሩ ለመጾም ያልቻሉት የታመመው፤ ከበሽታው ሲድን፣ ተጓዡም ከጉዞው ሲመለስ፣ ወላድም በሰላም ተገላግላ ጡት ካጠባች በኋላ ባልተጾመው ቀን ልክ በመጾም ሊያካክሱት ይችላሉ።

 ፍጹም መጾም የማይችል ደግሞ በጾሙ ቀናት ልክ የተቸገረውን ጾመኛን ከጾሙ በኋላ በማብላት ማካካስ እንደሚችል ፀሐፊው ያስረዳሉ።

ረመዳንና ቁርዓን

ቅዱስ ቁርኣን መውረድ ከጀመረበትን ቀን ጋር በመያያዙ የቅዱስ ቁርኣን ወር ነው ተብሎ ይጠራል። ቅዱስ ቁርኣንን መቅራትና በትእዛዛቱና በአስተምሮው መመራት የዘወትር ተግባር ቢሆንም፤ በረመዳን ወር ከሌሎች ወሮች በተለየ በግልና በቡድን ይቀራል። 

በዚህ የቁርኣን ንባብ በርካታ መለኮታዊ፣ መንፈሳዊ፣ ታሪካዊ፣ ሞራላዊ፣ ህጋዊ ወዘተ… የጸሎት ትምህርት እንዲታወሱና እንዲሰርጹ ዕድል ይፈጥራል። 

ጾሙ ትልቅ ትንሽ፣ ሃብታም ድሃ፣ ጠንካራ ደካማ ሳይለይበት ሁሉም የሚጾሙት በመሆኑ፣ በሁሉም ዘንድ የእኩልነት መንፈስ እንዲሰፍን ያግዛል። ረመዳን ሐብታሙ ድሃውን የሚያስብበት ወር በመሆኑ፣ ይህም ማህበራዊ የመረዳዳት ፋይዳ ያስገኛል።

የረመዳን ወር የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የወንድማማችነት ወዘተ ወርና የነዚህ እስላማዊ እሴቶች የስልጠና ወር ነው ማለት እንደሚቻል የሐይማኖቱ መሪዎች ያስረዳሉ።

የተራዊህ ሶላት፡-

‹‹ተራዊህ›› የሚለው የዓረብኛ ቃል ‹‹ማረፍ›› የሚል ትርጉም አለው። የተራዊህ ሶላት ሲባል አስር ረከዓ ሶላት እያረፉ መስገድ ማለት ነው። በአብዛኛው በረመዳን ወር ምሽት በመስጅድ ካልሆነም በኸለዋ በቡድን ይፈጸማል። በአገራችን በየሁለቱ ረከዓ መካከል በሚኖር የዕረፍት ጊዜ በለስላሳ ዜማ ወይም መንዙማ ፈጣሪን ያውቁበታል፣ ነብዩን ይዘክሩበታል፣ ዱዓ ያደርጉበታል።

ፍጡር፡-

በእስልምና ጾመኛን ማስፈጠር ልዩ ቦታና ደረጃ አለው። ያስፈጠረ ሰው በተግባሩ ከፈጣሪው ምንዳ እንደሚቸረው ያምናል። በዚህ መንፈሳዊ ምንዳ የተነሳ ሙስሊሞች ከጎረቤት፣ ከመንገደኛ፣ በተለይም ከችግረኛ ጋር ለማፍጠር ወይም ለማስፈጠር ይጣደፋሉ። በአንድ ማዕድ ዙሪያ ተሰባስበው ቤት ያፈራውን ይቃመሳሉ።

ሶደቃ፡-

ሶደቃ ለራስ፣ በህይወት ለሌለ የቤተሰብ አባል ወይም ለአንድ ለሚያውቁት ሰው ተብሎ ለተቸገሩ የሚሰጥ የምጽዋት አይነት ነው። ኃጢያቶችን ያነጻል፣ ወደፊት ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎችን ይታደጋል ተብሎ ይታመናል። በመሆኑም የፈጣሪ ጸጋ ለማግኘት ብዙ ሙስሊሞች የረመዳን ጾምን ይመርጣሉ። የረመዳን ወር ጸጋ በደረጃ የላቀ መሆኑን በማሰብ ሶደቃው በስፋት ይካሄዳል።

ፊዳያ፡-

‹‹ፊዳያ›› ሙስሊሞች በሕመም፣ በጉዞ፣ በእርጅና፣ በተለይ ሴቶች በእርግዝና፣ በወሊድና ልጅ በማጥባት ወዘተ ምክንያቶች የረመዳንን ወር በሙሉ ወይም በከፊል መጾም ሳይችሉ ሲቀሩ ላልጾሟቸው ቀኖች የተቸገሩትን የማስፈጠር የማካካሺያ ተግባር ነው። 

ከፋራህ፡-

በእስልምና አንድ ሰው በጾም ወቅት የተከለከሉ ሀላልም ሆኑ ሀራም የሆኑ ድርጊቶችን ሲፈጽም ኃጢዓት ይሆኑበታል። ከድርጊቶቹ የሚነፃበት ክፍያ ‹‹ከፋራህ›› ይባላል። የከፋራህ አይነቱና መጠኑ እንደ ድርጊቱ አይነት ይለያያል። ግለሰቡ ከሰራው ኃጢዓቱ ለመንጻት  መጾም ይጠበቅበታል። ካልቻለ 60 ችግረኞችን በማብላት ከፈጸመው ኃጢዓት መንጻት ይኖርበታል።

ዘካተል ፍጡር፡-

‹‹ዘካተል ፍጡር›› የረመዳን ወር የፍቺ ክብረ በዓልን ለማክበር አቅም የሌላቸው ሰዎች እንደ ሌሎቹ ተደስተው እንዲውሉ የሚሰጥ ግዴታ የሆነ ክፍያ ነው። ያልከፈለ ሰው የተሟላ ጾም እንደጾመ አይቆጠርለትም። ይህ ለተቸገሩት የሚሰጥ ክፍያ ብዙውን ጊዜ በአይነት የሚፈጸም ሲሆን እንደ ሁኔታው በገንዘብ ሊተካም ይችላል። በአይነት ሁለት እፍኝ ስንዴ ይኾናል። በገንዘብ ሲኾን የእህሉ ተመን በረመዳን ወር ገበያ የሽያጭ ዋጋ ይወሰናል።

ዘካተል ፍጡር በቤተሰብ አባላት ብዛት ላይ ያተኩራል። ለምሳሌ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አምስት አባላት ቢኖሩ አምስቱም የቤተሰቡ አባላት እያንዳንዳቸው10 ኪሎ ግራም ስንዴ ወይም የስንዴውን ዋጋ ለተቸገሩ ይሰጣሉ።

ኢደል ፍጡር፡-

‹‹ፍጡር›› የሚለው ቃል በመዝገበ ቃላዊ ትርጉሙ ጾም መፍታት ይሆናል። ‹‹ኢደል ፍጡር›› የሚለው ቃል ትርጓሜ ደግሞ የረመዳን ጾም እንዳለቀ ባሉት የሸዋል ወር ሶስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ የጾም ፍቺ አከባበር ነው። 

ጾሙም ሆነ የጾም ፍቺ በጨረቃ ዑደት ላይ በመመስረቱ ፍቺው በ30ኛው ወይም በ29ኛው ቀን ማግስት ሊሆን ይችላል። ከሁለቱ በአንዱ ቀን አንስቶ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ኢደል አልፍጡር በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

የመጀመሪያው ከጾም ፍቺ ቢያንስ አንድ ቀን አስቀድሞ ለተቸገሩ የጾም ፍቺ የሚሆን ስጦታ ይበረከታል። ስጦታው ዘካተል ፍጡር ይባላል። ስጦታው የግዴታ ሲሆን፣ መጠኑ በቤተሰብ አባል ብዛት ይወሰናል። ክፍያው በአብዛኛው በአይነት ማለትም ለምግብ አገልግሎት የሚውል እህል የሚሰጥ ሲሆን፣ ካልተቻለ ዑለሞች በሚያወጡት የወቅቱ የገበያ ተመን መሠረት ክፍያው ወይም ስጦታው በገንዘብ ሊሆንም ይችላል ።

ሁለተኛው የጾም ፍቺ ከአራቱም ማዕዘናት ሙስሊሞች አደባባይ በመገኘት የጾም ፍቺ ስግደት በጋራ ይፈጽማሉ። 

ሦስተኛው፣ በሦስቱ ተከታታይ ቀናት ፈጣሪን በማመስገን፣ እርስ በርስ በመጠያየቅና በመዘያየር ሚዛናዊ በሆነ አግባብ ከወትሮው በተለየ መንገድ በደስታና በፍስሃ ማሳለፍ ነው።

በዋዜማ ምሽት ሴቱም ወንዱም ለበዓሉ በድምቀት መከበር የየድርሻቸውን ዝግጅት ያደርጋሉ። የሚበላው የሚጠጣው ይሰናዳል። ሌሊቱ በጸሎት ይታለፋል። ንጋት ላይ ሁሉም ገላውን ተጣጥቦ፣ ጸአዳ ልብስ ለብሶ፣ ህጻን አዛውንት ሳይለይ ለስግደት አቅራቢያው ወደሚገኝ አደባባይ ተክቢራ እያለ ይወጣል ይላል ጽሀፉ። 

ከአደባባዩ ሥነ ሥርዓት በኋላ ሁሉም ወደየቤቱ በመመለስ ቀሪ ጊዜውን ከቤተሰቡ፣ ከጎረቤቱ ጋር ቡና በመጠጣት፣ አብሮ በመብላት፣ ዘመድና ወዳጅ በመጠየቅ ያሳልፋል።

እነዚህ ክንውኖች በእስልምና አስተምህሮ ከሚኖራቸው በረከትና ትሩፋት ባሻገር፣ በሰዎች መካከል ትውውቅ እንዲፈጠር፣ የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲዳብርና እንዲጠናከር አቅም ይፈጥራሉ።

ኢድ አል ፈጥር

ኢድ አል ፈጥር የረመዳን የጾም ወር ማብቂያን ተከትሎ በሸዋል ወር መጀመሪያ ላይ የሚከበር ታላቅ የእስልምና በዓል ነው። ሙስሊሞች ይህን ቀን በጋራ ተክቢራ በማድረግ፣ የኢድ ሰላት በመስገድ፣ በዓሉን በደስታ፣ በስጦታ፣ በቤተሰብ ጥየቃና በምግብ መጋራት ያሳልፋሉ፣ ይህም አላህ ለሰጣቸው ጥንካሬ የምስጋና ጊዜ ነው።

ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ማከበር የሚጀመረው ጎህ ሲቀድ በሚደረገው የጋራ የሰላት ሥነ ሥርዓት ላይ በመሳተፍ ነው።የጋራ ሰላት ወደሚደረግበት ስፍራ በጋራ ሲሄዱም “አላሁ አክበር” በማለት ተክቢራትን እያሰሙ ለፈጣሪ ምስጋና እያቀረቡ ነው።

በዓሉ በአብዛኛው ጣፋጭ ምግብ የሚበላበት በመሆኑ ‹‹የጣፋጭ ኢድ››ይታወቃል፡፡ በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ከቴምርና ሌሎች ጣፋጭ ነገሮች የተሰሩ ‹‹ማሙል›› በመባል የሚታወቁ ብስኩቶችን መመገብ የተለመደ ነው።

በአብዛኛዎቹ እስልምና ተከታይ አገሮች በዓሉን አክባሪዎቸ ጣፋጭ ነገሮችን በመያዝ ዘመዶችንና ጎረቤቶቻቸውን በመጠየቅ ያሳልፋሉ።

በዓሉን ሕጻናት አዲስ ልብስ ለብሰው ስጦታ እየተቀበሉ በዓሉን ተደስተው ያከብሩታል። ወጣቶች፣ጎልማሶችና አረጋውያን በተመሳሳይ ስሜት የሚያከብሩት ለሚቀጥለው ዓመት እንዲያደርሳቸው እየተመኙ ነው፡፡

መልካም የኢድ አል ፈጥር በዓል!!!

ኢድ አል ፈጥርበዓልረመዳን

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!