እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:50:52 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ

ወደ "ቀዳሚ ባለቤትነት እና ሉዓላዊ ጥበቃ" የተሸጋገረው ደህንነት

2 ደቂቃ ንባብ
ወደ "ቀዳሚ ባለቤትነት እና ሉዓላዊ ጥበቃ" የተሸጋገረው ደህንነት
ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ተሞክሮና ራዕይ ሞሮኮ ውስጥ በሚካሄደው ጂአይቴክስ አፍሪካ 2026 ተብሎ በተሰየመው መድረክ አቅርባለች።
1 / 2

የኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነት ወደ "ቀዳሚ ባለቤትነት እና ሉዓላዊ ጥበቃ" (Sovereign Proactivity)መቀየሩን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ)ገለጸ።

ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ተሞክሮና ራዕይ  ሞሮኮ ውስጥ በሚካሄደው ጂአይቴክስ አፍሪካ 2026 መድረክ አቅርባለች።

የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግሥት ሃሚድ በሞሮኮ እየተካሄደ ላይ ባለው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ጉባዔ ላይ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በሳይበር ደህንነት ረገድ የነበራት "ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ የማገገም" (Reactive Recovery) አካሄድ ተቀይሯል።

ዋና  ዳይሬክተሯ በዚህ"የማይበገር ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት አቅም መገንባት - Building a Cyber-Resilient Nation” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ስትራቴጂያዊ የመሪዎች የፓናል ውይይት ላይ የኢትዮጵያን ተሞክሮ አጋርተዋል። 

በዚህም ኢትዮጵያ በሳይበር ደህንነት ረገድ የነበራት "ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ የማገገም" (Reactive Recovery) አካሄድ ወደ "ቀዳሚ ባለቤትነት እና ሉዓላዊ ጥበቃ" (Sovereign Proactivity) መቀየሩን አመላክተዋል። 

ይህም የሳይበር ጥቃቶች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ፣ የሰው ኃይልና መሰረተ-ልማት የመገንባት ስትራቴጂ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ዲጂታል ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ተፈጻሚ መሆኑን፣ የመሠረተ ልማት ተቋማት የሳይበር ደህንነታቸውን እንዲጠብቁ የሚያስገድድ ዓዋጅ መዘጋጀቱን፣ እንዲሁም የሕዝብ ቁልፍ መሰረተ ልማትና የሉዓላዊ የመንግስት ክላውድ (Sovereign Government Cloud) ግንባታን በዋቢነት ጠቅሰዋል። 

በውጭ ቴክኖሎጂዎች ላይ የነበረው ጥገኝነትና የሰው ኃይል ፍልሰትን በመቀነስና የውጭ ቴክኖሎጂዎችን ከመግዛት ባለፈ፤ የሀገር በቀል የሳይበር ደህንነት ምርቶችን ወደ ማልማት  መሸጋገሯንም ወይዘሮ ትዕግሥት ተናግረዋል።

በዘርፉ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ ትብብር የቴክኖሎጂ ሽግግርና የጋራ መረጃ ለመለዋወጥ አስፈላጊ ቢሆንም፣ የሀገርን የዳታ ሉዓላዊነት በማይነካና ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዙና የሰውን ሥነ-ልቡና መሠረት ያደረጉ የማህበራዊ ምህንድስና (Social Engineering) ጥቃቶች እያደጉ መምጣታቸውን ገልጸው፣ ይህንን ለመከላከል አኳያ የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊና ለማሳደግና ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ባሕል ለመገንባት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሳይበር ደህንነት መመዘኛ (Global Cyber Security Index - GCI) ወደ ደረጃ ሦስት (Tier 3) ከፍ ማለቷን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ደረጃውን በቀጣይነት በማሳደግ የኢትዮጵያን የዲጂታላይዜሽን ጉዞ በአስተማማኝ የሳይበር ደህንነት ላይ በመመስረት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ለተሳታፊዎቹ አስረድተዋል። 


የሳይበር ደህንነትኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂሳይንስና ቴክኖሎጂ

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!