እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
08:24:46 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ኢኮኖሚ

የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈተና

4 ደቂቃ ንባብ
የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈተና
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት 80 ዓመታት የተለያዩ ተግዳሮችን ተቋቁሞ በውጤታማነት በአሀጉሩ ቀዳሚ ሆኖ የወጣ አየር መንገድ ነው፡፡ ሰሞኑን በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የተከሰተው ጦርነት በገቢው ላይ ያሳደረበትን ተጽዕኖ ተቋቁሞ የተያያዘውን የዕድገት ጉዞ ይቀጥላል ይሆን የሚል ጥያቄ መነሳት ጀምሯል፡፡

የመካከለኛው ምሥራቅ ጂኦ ፖለቲካዊ መልክዓ ምድር በዚህ ዓመት አጋማሸ በእጅጉ ተቀይሯል፡፡ በመሆኑም በቀጣናው የተፈጠረው ግጭት በዓለም አቪዬሸን ኢንዱስትሪ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ በዘርፉ ባለሙያዎች እየተገለፀ ይገኛል፡፡ በዚህም ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንዱ ነው፡፡

በአፍሪካ ግዙፉና ውጤታማው አየር መንገድ በግጭቱ ሳቢያ ገቢው እየተጎዳ መሆኑን በያዝነው ሳምንት ይፋ አድርጓል፡፡ እስከ የካቲት 30/2018 ድረስ ባለው ጊዜ ወደ137 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ አጥቻለሁ ብሏል፡፡

ለበረራዎቹ መቋረጥ ዋንኛው መንስዔ አሜሪካና እሥራኤል በቅንጅት የኢራንን ወሳኝ የመሠረተ ልማትንና ወታደራዊ ተቋማትን ለማውደምና መሪዎቻቸውን ለማስወገድ የከፈቱት ዘመቻ አድማሱን በማስፋት በርካታ የአካባቢውን አገሮች በመንካቱ ነው፡፡ በዚሀም ሚሳይሎችና ድሮኖችን ባካተተ ጦርነት ሳቢያ የንግድ በረራዎች እንዲቋረጡ አድርጓል፡፡

በዚህም ምክንያት የአየር መንገዱን ትርፋማነትና ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል። ጦርነቱ አየር መንገዱ አፍሪካን ከመካከለኛው ምስራቅ አልፎም  ከእስያና ከአውሮፓ ጋር በማገናኘት ይጫወት የነበረውን ሚና እንዳደናቀፈበት የተቋሙ ኃላፊዎች ገልፀዋል፡፡

ወደ ሁለተኛ  ሣምንት የተሸጋገረው ጦርነት የአየር መንገዱን የፋይናንስና የበረራዎች መረጃ አሉታዊ ምሰሎች ከዋናው መሥሪያ ቤቱ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ማሳየት ጀምረዋል፡፡ የአየር መንገዱ በረራዎቹ መስተጓጎል በቀጣናው የተፈጠረው የጂኦ ፖለቲካ ቀውስ ተጎጂ መሆኑን በግልጽ አሳይተዋል፡፡

አየር መንገዱ የገጠመው የመጀመሪያው ችግር ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚያደርጋቸው በረራዎች ማቆማቸው ነው፡፡ ይህም ቢያንስ ወደ 10 ከተሞች የሚያደርጋቸወን በረራዎች እንዲያቋርጥ አድርገውታል፡፡ መሥመሮቹ ለአየር መንገዱ የጀርባ አጥንት የሆኑ ወደ አገሮቹ የሚጓጓዙ ሠራተኞችንና የንግዱንማህረሰብ በማገናኘት ላቅ ያለ ሚና ያላቸው ናቸው፡፡

በቀጣናው ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት አየር መንገዱ ከፍተኛ ምልልስ የሚያደርገባቸው ቁልፍ ከተሞች ነበሩት፡፡ ከነዚህም በቁጥር አንድ ደረጃ የተቀመጠው ወደ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ዱባይ ከተማ የሚያደርገው ነው፡፡ ዱባይ በቀን በርካታ በረራዎች የሚስተናገዱበት መሥመር ነበር፡፡ አሁን በረራዎች የሚስተናገዱበት ሳይሆን፤ ሚሳኤሎች የሚወናጨፉበትና የጸጥታ ስጋት ያለበት ሆኗል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ በተለይ የዳማም ከተማ በሣምንት እስከ 38 በረራዎች የሚስተናገዱበት መሥመር ነበር፡፡ መሥመሩን ስደተኛ ሠራተኞችንና ነጋዴዎችን የሚያገናኝ ሁነኛ ገበያው ሆኖ ቆይቷል፡፡

ወደ ቴል አቪቭ፣ እሥራኤል በሣምንት 18 ያህል በረራዎች ይደረጉ ነበር፡፡ መሥመሩ ጦርነቱ እንደተቀሰቀሰ ወዲያውኑ በረራም ገቢም የቀረበት ሌላኛው መዳረሻ ሆኖ ቀርቷል፡፡

ወደ አማን፣ ቤይሩትና ሌቫንት ከተሞች የሚካሄዱ በረራዎች ውሱን ቢሆኑም፤ በአየር መንገዱ ሥራ አፈጻጸምና ገቢ ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸው ግልጽ ሆኖ ይታያል፡፡

በአጠቃላይ አየር መንገዱ ወደ አካባቢው አገሮች ያደረጋቸው የነበሩትን በቀን በአማካይ 15፣ በሣምንት ደገሞ ከ100 በላይ በረራዎች ለመሰረዝ ተገዷል፡፡ አየር መንገዱን በቀጠናው መሪ ያደረገውን ለጭነት አገልግሎት ያደረጋቸው የነበሩ በረራዎች ሲታከሉበት በሣምንት ከ160 በላይ በረራዎች ቀርተውበታል፡፡

በበረራዎቹ መስተጓጎል የሚጎዳው አየር መንገዱ ብቻ አይደለም፡፡ በሣምንት ያጓጉዛቸው የነበሩት ከ40ሺህ እስከ 50ሺህ የሚደርሱ መንገደኞች ቸግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡ አብዛኛዎቹ በሌሎች በረራ ባላቋረጡ አየርመንገዶች ማለትም እንደ ኢቲሃድ እና ካታር አየር መንገዶች ከፍተኛ ዋጋ ከፍለው ለመጓጓዝ ይገደዳሉ፡፡

የስትራቴጂክና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል በጦርነቱ የመጀመሪያዎቹ 100 ሰዓታት ብቻ 3ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወጪ ማስወጣቱን አስታውቋል፡፡ ጦርነቱ አሁን ባለበት ሁኔታ በዲፕሎማሲዊ መንገዶች የሚፈታበት ሁኔታ አጠራጣሪና በረራዎች ፈጥነው የሚጀምሩበት መንገድ ይኖራል ለማለት እንደሚያስቸግር አመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከበረራዎቹ ያጣው 137 ሚሊዮን ዶላር  ቀላል የሚባል ገቢ አይደለም፡፡ የበረራዎቹ መቅረት የሚያሳድርበትን ተጽዕኖ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ የአየር መንገዱ የቢዝነስ ሥራ አስኪያጅ ለማ ያዴቻ መካከለኛው ምሥራቅ የነዳጅ አምራችና ሽያጭ ማዕከል በመሆኑ የነዳጅ ዋጋ እንደሚጨምር ይገልፃሉ፡፡ ይህም ገቢ እያጣ ላለው አየር መንገድ በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጉዳት ይደርስበታል ይላሉ፡፡ 

በተጨማሪም ግጭት በተፈጠረባቸወ አገሮች አየር ላይ የሚደረጉ በረራዎች የመድን ክፍያ እንደሚጨምርም አስረድተዋል፡፡ ይሄኛው ወጪ የሚሸፈነው አንድም በአየር መንገዱ አልያም በመንገደኛው ይሆናል፡፡ ክፍያው ወደ መንገደኛው ከተሸጋገረ ደግሞ የአውሮፕላን መንገደኞችን የሚያሸሽ ሊሆን ይችላል በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡

የአየር መንገዱ የጭነት አገልግሎት ሌላው ጉዳት የደረሰበት ክፍል ነው፡፡ አበባ፣ ጨርቃ ጨርቅና ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ከአፍሪካና ከባህረ ሰላጤው አገሮች ስለማያጓጓዝ፡፡ የበረራዎቹ መስተጓጎል የአቅርቦት ሰንሰለቱን ያቋርጠዋል፡፡ በዚህም ትርፋማ የነበረውን ዘርፍ ገቢ እንዲያጣ አድርጎታል፡፡

አየር መንገዱ ከገጠሙት ችግሮች ለመውጣት ዋና ሥራ አስፈጻሚው መሥፍን ጣሰው የሚመሩት ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት የተካተቱበት ቡድን አዋቅሯል፡፡ ቡደኑ ለመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ተመድቦ የነበረው ሀብት ወደ ሌሎች እያደጉ የመጡ ገበያዎች እንዲዞር ወስኗል፡፡

በዚህም ወደ አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካና አፍሪካ ውስጥ የሚደረጉ በረራዎች እንዲስፋፉና ድግግሞሻቸው መጨመርን አማራጭ መንገድ አድርጎ አስቀምጧል፡፡

አየር መንገዱ ይህን ይበል እንጂ፤ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ለአየር መንገዱ የመካከለኛው ምሥራቅ በረራዎች መዳረሻዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ መንገደኞችን ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚያሸጋግርባቸው ድልድዮቹ ናቸው ይላሉ፡፡ እነዚህን መዳረሻዎች ካልተጠቀመባቸው የነበረውን አንጻራዊ ጥቅም ያጣል ይላሉ፡፡ በዚህም የአውሮፓ አየር መንገዶች መዳረሻዎቹን የሚጠቀሙበት ዕድል ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን የገጠመው ችግር የአየር በረራና ሰላም ምን ያህል የተቆራኙ መሆናቸውን ፍንትው አድርጎ አሳይቶታል፡፡ ጉዳዩ በሣምንት 137 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የማጣት ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖና በአፍሪካ አቪየሽን ዕድገት ላይ በሚያሳድረው ጥላ ሊታይ ይችላል፡፡

ቀጣዮቹ ሣምንታት አየር መንገዱ የቀየሳቸው ስትራቴጂዎች አዋጪ መሆን አለመሆናቸውን የሚያመላቱ ሆነው ይታያሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ስትራቴጂዎቹ የአፍሪካውን ግዙፍ አየር መንገድ ከቀውስ ያወጣሉ ወይስ በተራዘመ ወቅት በቀውሱ ውስጥ ያቆዩታል የሚለውን አመላካች ይሆናሉ፡፡

አየር መንገድየኢትዮጵያ አየር መንገድ

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!