እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
08:22:25 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ኢኮኖሚ

የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ዓዋጅ ፀደቀ

2 ደቂቃ ንባብ
የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ዓዋጅ ፀደቀ
ምክር ቤቱ ረቂቅ ዓዋጁን የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ዓዋጅ ቁጥር 1411/2018 ተብሎ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል፡፡
1 / 2
 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻሻለውን የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ዓዋጅን በሙሉ ድምፅ አፀደቀ።

ምክር ቤቱ ዓዋጁን ያፀደቀው ዛሬ ባካሄደው በአምስተኛው የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ ነው።

የተሻሻለውን የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ ዓዋጅን በሚመለከት ከግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን ሪፖርትና ውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አፅድቋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ ሪፖርቱንና የውሳኔ ሃሳቡን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በግብርና ላይ የተመሰረተ መሆኑንና በዘርፉ ምርትን በብዛት፣ በጥራትና በቀጣይነት ለማሳደግ የግብርና ኤክስቴንሽን ከፍተኛ ሚና አለው፡፡

ለዚህም ከሚያግዙት መካከል የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን ተደራሽነት ለማስፋት፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ዓዋጅ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ዓዋጁ በዚህ ረገድ የግብርና ቴክኖሎጂን ማስተዋወቅና ጥቅም ላይ ማዋል እንዲሁም የግብርና ቢዝነስን ለማስፋት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

ረቂቅ ዓዋጁ በመንግሥት ብቻ የሚሰጠው የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት በቂ ባለመሆኑ ወቅቱ የሚጠይቀውን የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ሥርዓት እንዲዘረጋ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር ሰብሳቢው አመላክተዋል፡፡

በዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽን የሚያማክሩና የመረጃ ቅብብሎሽ አገልግሎት የሚሰጡ የግል ባለሀብቶች ፣መንግሥታዊ የሆኑና ያልሆኑ ድርጅቶች እየታዩ በመሆኑ በግብርና ኤክስቴንሽን ውስጥ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት አሰጣጡ ጥራትና ፍትሃዊነት ቁጥጥር ትኩረት የሚሻ በመሆኑ አገልግሎት የሚሰጠው በተመዘገበና የብቃት ማረጋገጫ ባገኘ አገልግሎት አቅራቢ መሆን እንደሚኖርበትየአሰራር ሥርዓት እንደተቀመጠም አብራርቸዋል፡፡

የግብርና ኤክስቴንሽን መሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን ማዘመን በመንግሥት ላይ ብቻ በመውደቁ በሚጠበቀው ደረጃ እርካታ ያልተገኘበትን የተጠቃሚዎች ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የግብርና ኤክስቴንሽን ፈንድ ማቋቋም ረቂቅ ዓዋጁ እንዳካተተ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡

በግብርና ባለሙያዎች ብቻ ይሰጥ የነበረው የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት አሁን ላይ የምርት መጠንና ምርታማነትን ለማሳደግ በቂ ምላሽ ባለመስጠቱ ችግሩን ለማቃለል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎቱን ማሻሻልና ማዘመን አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፣ ከግብርና ምርምር የሚገኙና ከውጭ የሚመጡ ቴክኖሎጂዎችን የግብርና ባለሙያው ለአርሶ አደሮች በተግባር ማሳ ላይ እያሳዩና እያስተማሩ አገልግሎት እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡

በአገሪቱ የግብርና ኤክስቴንሽን ተደራሽነት ከ36 በመቶ በላይ አለማለፉን ጠቁመው፣ ረቂቅ ዓዋጁ ይህንን ክፍተት እንደሚሞላ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ረቂቅ ዓዋጁ መንግሥታዊ ያልሆኑ የአገልግሎት ተዋንያን ሕጋዊነትን በጠበቀ መልኩ፣ ተጠያቂነት በሰፈነበትና ጥራቱ በጠበቀ ሁኔታ መንግሥትንና አርሶ አደሩን በመደገፍ የግብርና ልማቱን በሚገባ እንደሚያሳልጥ ጠቁመዋል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ በረቂቅ ዓዋጁ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ ዓዋጅን፣ ዓዋጅ ቁጥር 1411/2018 ተብሎ ሥራ ላይ በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል፡፡


የግብርና ኤክስቴንሽንግብርና

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!