እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
05:14:59 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ

የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት ያረጋገጡት ግኝቶች

2 ደቂቃ ንባብ
የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት ያረጋገጡት ግኝቶች
በአፍሪካ የሰው ዘር አመጣጥ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የመረጃ ክፍተት የነበረበትን ከ900 ሺህ እስከ 200 ሺህ ዓመታት ያለውን ጊዜ የሚዘክሩ አዳዲስ መረጃዎችን ይዟል።
በኢትዮጵያ አፋር ስምጥ ሸለቆ በመካከለኛው አዋሽ የምርምር ፕሮጀክትየጥንታዊ ሆሞ ሳፒየንስ ቅሪተ አካላት መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የባለሥልጣኑ የአጥኚ ቡድን ዛሬ የሰው ልጅ የዝግመተ ለውጥ ጉዞንና ጥንታዊ የአኗኗር ዘይቤን የሚያሳዩ አዳዲስ የአርኪዮሎጂ ግኝቶችን ይፋ አድርጓል።

በዮናስ በየነ (ዶ/ር) የተመራውና ከ24 እገሮች የተውጣጡ ሳይንቲስቶች የተሳተፉበት ቡድን ጥናቱ የረጅም ዓመታት ምርምር ውጤት መሆኑን ገልጿል።

ጥናቱ ከ100ሺህ ዓመታት በፊት ይኖሩ የነበሩ ዝርያዎችን ለማወቅ እንዳስቻለና ኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ዳግም እንዳረጋገጠ ተመላክቷል፡፡

በአፍሪካ የሰው ዘር አመጣጥ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የመረጃ ክፍተት የነበረበትን ከ900 ሺህ እስከ 200 ሺህ ዓመታት ያለውን ጊዜ የሚዘክሩ አዳዲስ መረጃዎችን መያዙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው በኢትዮጵያ እየተደረጉ በሚገኙ ምርምሮች የተለያዩ የጥናት ግኝቶች ለዓለም እየተበረከቱ ሲሆን፥ ዛሬ ይፋ የተደረገው የምርምር ውጤት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል።

በምርምሩ የሆሞ ሳፒየንስ የሰው ዘር አመጣጥን፣ ሰዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩ የድንጋይ መሣሪያዎችን፣ የሰው ዘር ቅሪተ አካላትንና የእንስሳት ቅሪቶች መገኘታቸውን አብራርተዋል።

እነዚህ አዲስ ሳይንሳዊ የአርኪዮሎጂ ግኝቶች ኢትዮጵያ አሁንም የሰው ልጅ ዘር መገኛ መሆኗን ዳግም ለዓለም ያረጋገጡ ክስተቶች መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ      አስታውቀዋል።

በበበአፋር ስምጥ ሸለቆ ሀሊቢ በተባለ ስፍራ የተገኙ ወሳኝ የአርኪኦሎጂ እና የፓሊዮአንትሮፖሎጂ ግኝቶችን የሚተነትን ሳይንሳዊ ጽሑፍ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባለው “ፕሮሲዲንግስ ኦፍ ዘ ናሽናል አካዳሚ ኦፍ ሳይንስ” መጽሔት ላይ ዛሬ ታትሞ መውጣቱን ተመራማሪው ዮናስ በየነ (ዶ/ር) አስረድተዋል።

በሀሊቢ አካባቢ የተደረገው ይህ ጥናት ከ100 ሺህ ዓመታት በፊት የነበረውን የሰው ልጅ አኗኗርና አካባቢያዊ ሁኔታ የሚፈትሹ አዳዲስ መረጃዎችን ይፋ ማድረጉን ተናግረዋል።

በጥናቱ በጥንቃቄ የተሰሩና ለተለያዩ አገልግሎቶች ይውሉ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የድንጋይ መሣሪያ ስብስቦች የሰው ልጅ የቴክኖሎጂ እድገት ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።

በወቅቱ አካባቢው የዛሬውን በረሃማ ገጽታ ሳይሆን፤ ለምለምና ጫካማ እንደነበር የሚያሳዩ የጉሬዛ፣ የዝንጀሮ፣ ቀንድ ያላቸው እንስሳት፣ የአይጦችና የአዕዋፍ ቅሪቶች መገኘታቸውንም በማሳያነት አቅርበዋል።

ይህም በጥንታዊው የአዋሽ ወንዝ አካባቢ የነበረውን የተመቻቸ የተፈጥሮ ሁኔታና የሰው ልጆች እንቅስቃሴ ያሳያል ነው ያሉት ለኢዜአ፡፡

ግኝቱ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን በተጨባጭ ከማረጋገጡም በላይ፣ ጥንታዊ ሆሞ ሳፒየንሶች በአፋር ስምጥ ሸለቆ የነበራቸውን የኑሮ ሁኔታ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የአካባቢ ተጽዕኖ በዝርዝር ማሳየቱን ተመራማሪው ገልጸዋል።
 
ሳይንስና ቴክኖሎጂአርኪዮሎጂ

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!