
በግብርናው ዘርፍ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብና ሥነ-ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ የልማት ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ድርሻቸው የላቀ መሆኑ ተመላከተ፡፡
የእንስሳትና ዓሳ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት የእንስሳት ዘርፉን በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና የሥራ ዕድል በመፍጠር ሚናውን እየተወጣ ይገኛል፡፡
ፕሮጀክቱ የእንስሳት ዘርፍን ምርታማነት ለማሳደግና የሚጠበቀውን ግብ ለማሳካት በመደበኛው የእንስሳት ልማትና በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ለተመዘገበው ውጤት አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና አሳ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ ቶማስ ቸርነት (ዶ/ር) በተመረጡ የወተት፣ የእንቁላልና ዶሮ፣ ዓሳ፣ ሥጋና የእንስሳት መኖ እሴት ሰንሰለት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት በተመረጡ እሴት ሰንሰለቶች ላይ የጋራ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖችን በማደራጀት፣ ኅብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖችን በመመስረትና በመደገፍ ምርታማነትንና ኮሜርሻላይዜሽንን ማሳደጉንም ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ከምርት ጀምሮ እስከ ገበያ ያለውን እሴት ሰንሰለት በማጠናከር የገበያ ትስስር መፍጠርና ተቋማዊ አደረጃጀትን በማጠናከር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።
አርሶ አደሩ የእንስሳት ኤክስቴንሽኑ ባለቤት እንዲሆን የአርሶ አደር የመስክ ትምህርት ቤትን ተግባራዊ በማድረግና በማላመድና የእንስሳት ኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲስፋፋ መደረጉንም አስተባባሪው አስረድተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በሥራ ዕድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከሦስት ሚሊዮን በላይ ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚዎች ማድረጉን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በቤተሰብ ደረጃ የምግብና ሥነ-ምግብ ዋስትናን በማሻሻል ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ መፍጠሩም ተገልጿል፡፡
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!