
የዲጂታል ፋይናንስ ምህዳርን ተከትሎ የሚታዩ ስጋቶችን በጋራ መከላከልና ዘላቂ መፍትሄዎችን ማመላከት እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በዘርፉ የሚሰሩ አካላት አመላከቱ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት ያዘጋጁት "ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ፋይናንስ ለሀገራዊ ዕድገት"በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
ውይይቱ የዘርፉን ቁልፍ ባለድርሻ አካላትና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ዛሬ በአንድ መድረክ አገናኝቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር)፤ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ያለውን ፋይዳ በመጥቀስ፣ ሥርዓቱ ግን በሰላምና በደህንነት ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሳይበር ወንጀል ስልቶች በየቀኑ የሚቀያየሩ በመሆናቸው ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች ወንጀሎች ለመቆጣጠር በሚያስችል መልኩ በየጊዜው እንዲያዘምኑ አሳስበዋል።
ጉዳዩ በሚመለከታቸው ተቋማት መካከል ያለው ቅንጅት በቴክኖሎጂ የተደገፈና ወደ ተግባር የተቀየረ መሆን እንዳለበት ገልጸው፤ ቋሚ ኮሚቴው ይህንን የቅንጅት ሥራ በቅርበት እንደሚከታተልና ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ ፤ የዲጂታል ፋይናንስ ምህዳሩን ከስጋት ነፃ ማድረግ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና ለዜጎች ደህንነት ወሳኝ መሆኑ አስረድተዋል።
የዲጂታል ፋይናንስን የሳይበር ደህንነት ማረጋገጥ የአንድ ተቋም ድርሻ ብቻ ሳይሆን፤ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ውጤት መሆን እንዳለበት በመጠቆም።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ በበኩላቸው፤ ባንኩ የፋይናንስ ተቋማትን ደህንነት ለማረጋገጥ የቁጥጥር ሥርዓቱን ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ጋር እያጣጣመ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋማት ጠንካራ የቴክኖሎጂ አቅምና የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲገነቡ የሚያስገድዱ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እየተተገበሩ ነው ብለዋል ።
በሕግ አስከባሪዎችና በአገልግሎት ሰጪዎች መካከል ያለውን የተቀናጀ የመረጃ ልውውጥ ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ናቸው።
ይህም ወንጀለኞችን በአፋጣኝ ለይቶ ለሕግ ለማቅረብና የተደራጁ የዲጂታል ጥቃቶችን ለመቀልበስ ቁልፍ መሣሪያ እንደሆነ አመላክተዋል ።
የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ሞባይል መኒ ቢዝነስ ኦፊሰር አቶ ብሩክ አድኃና፤ የዲጂታል ማጭበርበርን የሳይበር ደህንነት መዋቅሮችን በመፍጠርና የዲጂታል ማንነት ማረጋገጫ ሥርዓቶችን በማዘመን በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሥዩም ዳምጠው በበኩላቸው፤ የማንነትና የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበርን ለመከላከል ተቋማት የቴክኖሎጂ አቅማቸውንና የደህንነት ማዕቀፎቻቸውን በየጊዜው ማጠናከር አለባቸው ይላሉ።
ባንኩ የደንበኞችን መረጃና የዲጂታል ሀብት ከአጭበርባሪዎች ለመጠበቅ የሚያስችሉ ስትራቴጂያዊ የክትትል እርምጃዎችን በቁርጠኝነት እየተገበረ መሆኑንም አብራርተዋል።
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!