እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:50:52 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ሕግና ፍትሕ

የዲጂታል ፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል የሕግ ማዕቀፎችን ማጠናከር ያስፈልጋል

2 ደቂቃ ንባብ
የዲጂታል ፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል የሕግ ማዕቀፎችን ማጠናከር ያስፈልጋል
በመድረኩ ላይ “ሀገራዊ የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበር ወንጀል ዳሰሳ ጥናት” በሚል ርዕሰ ጥናት የቀረበ ሲሆን፣በጥናቱም በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበር ያለበትን ደረጃና በቀጣይ መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች ተዳሰዋል።
1 / 3

የዲጂታል ፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል የሕግ ማዕቀፎችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የፍትሕ ሚኒስትሯ ሐና አርአያ ሥላሴ አሳሰቡ።

የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበርን ለመከላከል የሚያስችል ሀገራዊ የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።

መድረኩን ያዘጋጁት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ነው።

በመድረኩ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበር ወንጀል ለመከላከል የሚያስችሉ ስትራቴጂያዊ መፍትሄዎች ላይ አትኩሯል።

በመድረኩ ላይ “ሀገራዊ የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበር ወንጀል ዳሰሳ ጥናት” በሚል ርዕሰ ጥናት የቀረበ ሲሆን፣በጥናቱም በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበር ያለበትን ደረጃና በቀጣይ መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች ተዳሰዋል።

ጥናቱ በተለይ ከሕግ፣ ከቴክኖሎጂ፣ ከአደረጃጀትና ከአሰራር ሥርዓት አንፃር መስተካከል ያለባቸውን ነጥቦች በመጠቆም፣ ሀገራዊ የመከላከል አቅምን የሚያጎለብቱ ምክረ-ሃሳቦችን አቅርቧል።

ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ  ተወካዮች የተሳተፉበት የፓናል ውይይት ባካተተው በዚህ መድረክ በቀጣይ በኢትዮጵያ የሚከሰቱ የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበር ወንጀሎችን በቅንጅት ለመከላከል የሚያስችሉና ለፖሊሲ ግብዓቶች የሚሆኑ ጠቃሚ ሃሳቦች መነሳታቸውን ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል ።

"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂን ስኬታማ ለማድረግ አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ፋይናንስ ሥነ-ምህዳር መፍጠር ወሳኝ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተገልጿል። 

ከዚህ አኳያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታው ያለ ምንም የደህንነት ስጋት እንዲቀጥል የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም የጸጥታና የደህንነት ተቋማትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ተመላክቷል።

ሚኒስትሯ  መድረኩን  ሲከፍቱ  እንዳስገነዘቡት የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበር ወንጀልን ለመከላከል የሕግ ማዕቀፎችን ማጠናከር አስፈላጊና ዘመኑ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው። 

"ዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበር የዜጎችን ሀብት ብቻ ሳይሆን፤ በሀገሪቱ የፋይናንስ ስርዓት ላይ ያለውን እምነት የሚሸረሽር በመሆኑ፣ ከቴክኖሎጂው እድገት ጋር የሚራመዱ ጠንካራ የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ በትኩረት መስራት ይገባል" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግሥት ሐሚድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ በምታደርገው ጉዞ የሳይበር ደህንነት ዋነኛው ምሰሶ መሆኑን ተናግረዋል። 

"የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት መጨመር ለዜጎች ምቾትን ቢፈጥርም፣ በዚያው ልክ የማጭበርበር ወንጀሎች ስጋት እየሆኑ መጥተዋል። ስለሆነም ቴክኖሎጂን ከጥቃት የመከላከል አቅማችንን ማሳደግና የዜጎችን ንቃተ-ሕሊና ማጎልበት የህልውና ጉዳይ ነው" ብለዋል።



 






ሕግና ፍትሕወንጀል መከላከልዲጂታል ወንጀሎች

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!