እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:51:49 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ኢኮኖሚ

የግብርናውን ሽግግር ለማፋጠን የተዘረጋው መርሐ ግብር

3 ደቂቃ ንባብ
የግብርናውን ሽግግር ለማፋጠን የተዘረጋው መርሐ ግብር
የአነስተኛ ባለይዞታ አርሶ አደሮችን ገቢ በመጨመር፣ የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ዋስትናንና መርሐ ግብሩ አገራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል
1 / 3
ኢትዮጵያ ለዘመናት ተቆራኝቷት ከኖረው ተረጂነትና ልመና በመላቀቅ በምግብ ሰብል ምርት ራሷን ለመቻል ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡

ይህንንም ጥረት ከሚያግዙት አንዱ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ መርሐ ግብር ነው፡፡

የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ መርሐ ግብር በግብርና ሚኒስቴር ከሚሰሩ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች መካከል አንዱና በዓለም ባንክ በጀት የሚደገፍ ነው፡፡

መርሐ ግብሩ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2022 እስከ 2029 የሚካሄድ ሲሆን፥ የግብርና ዕድገት ፕሮግራም አንድና ሁለት ስኬቶችን በማስቀጠል የአገሪቷን የምግብ ሥርዓት ለማጠናከር ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ የሚገኝ መርሐ ግብር ነው፡፡

መርሐ ግብሩ በሰብል፣ በሆርቲካልቸር፣ በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት እንዲሁም በአነስተኛ የመስኖ አወታሮች ግንባታ፣ በገበያ ማዕከላትና አነስተኛ ድልድዮች ግንባታና በዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦት ተጨባጭ ድጋፍ በማድረግ የግብርናውን ሽግግር በማፋጠን ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

የምግብ ሥርዓትን የማሻሻልና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ አቅምን የመጨመር ዓላማን ያነገበ ነው። መርሐ ግብሩ፡፡

በአሥር ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች በ183 ወረዳዎች ውስጥ በ4ሺህ301 ቀበሌዎች በመተግበር 4ነጥብ 1 ሚሊዮን አባ/እማ ወራዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡

መርሐ ግብሩ በዋነኝነት የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የእሴት መጨመርንና የገበያ ተወዳዳሪነትን ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ የሚገልጸው የግብርና ሚኒስቴር መረጃ፤ በዚህም የአነስተኛ ባለይዞታ አርሶ አደሮችን ገቢ በመጨመር፣ የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ዋስትናንና አገራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል ይላል፡፡

በአራት ቁልፍ ክፍሎች የተዋቀረ መርሐ ግብር ሲሆን፥ ከነዚህም የግብርና አገልግሎትና የፈጠራ ሥርዓትን ማሻሻል አንደኛው ክፍሉ ነው፡፡

የግብርና አገልግሎት ቅልጥፍናንና ተደራሽነትን ማሳደግና የግብርና ቴክኖሎጂን ማመንጨትና የምርምር ሥርዓትን መለወጥ ሌላው ክፍል ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የተደራጀው የአነስተኛና የጥቃቅን መስኖ መሰረተ-ልማትን ማስፋፋት ክፍል ነው፡፡

የአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች መስኖ መሠረተ-ልማት መገንባት፥የመስኖ ውሃ አያያዝና የመስኖ መሠረተ-ልማት አስተዳደር የገበያ ማዕከላትንና አነስተኛ ድልድዮችን መገንባት፥የገበያ ልማት በቡድን የተደራጁ አንተርፕራይዞችን ማጠናከርና ማቋቋም በማካተት ይንቀሳቀሳል፡፡

ለሥርዓተ ምግብና ለፕሮግራም አስተዳደር አሰቻይ ሁኔታዎችን ማሻሻል የተባለው አራተኛው ክፍል ሲሆን፥
የፕሮግራም አስተዳደርና የፕሮግራም ክትትል፣ ግምገማ እንዲሁም ትምህርትን ያካትታል፡፡

እነዚህ ክፍሎች ተሰናስለው አካታች የምግብ ሥርዓትንና አቅምን ለመገንባት ምቹ ሁኔታን በስፋት ይፈጥራሉ ተብሎም እየተሰራባቸው ነው፡፡

በተያያዘም በገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት" በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የፓናል ውይይት በአዳማ ተካሂዷል፡፡ 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ(ዶ/ር) በፓናል ውይይቱ ባስተላለፉት መልዕክት ባለፉት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ በምግብ ራስን መቻል፣ ተኪ ምርትን ማምረት፣ ወደ ዉጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን ምርታማነት ማሳደግና በግብርናው ዘርፍ የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡ 

ፕሮግራሙ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከተረጂነት ወደ ትርፍ አምራችነት እንዲቀየሩ በማድረግ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

"ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉአላዊነት እና ክብር" በሚል ርዕስ ለፓናል ውይይቱ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ(ዶ/ር ) አቅርበዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የቆየች ሀገር ብትሆንም ተረጂነትና ልመናን ለማስቀረት የነበረው የታሪክ ስብራት የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ሳይችላት እንደቆየ በማመላከት።

ፕሮግራሙ በ10 ክልሎችና አንድ ከተማ አስተዳደር 490 ወረዳዎች ላይ የሚተገበር ሲሆን፥ በፕሮግራሙ 859 ሺህ 685 አባወራዎች/እማወራዎች ወደ ትርፍ አምራችነት መቀየሩ ተገልጿል፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎችና የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡


ኢኮኖሚግብርናየምግብ ዋስትና

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!