እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:43:47 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ኢኮኖሚ

ለወጣቶች ሥራ የፈጠረው ማዕከል

1 ደቂቃ ንባብ
ለወጣቶች ሥራ የፈጠረው ማዕከል
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን አድዓ ወረዳ የሚገኘው ጎዲኖ የተቀናጀ የግብርና ማዕከል ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡ 

ማዕከሉ የዶሮ እርባታ ያካሂዳል፤በተጓዳኝም ለአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የሚሆኑ ችግኞችን ያፈላል።

ማዕከሉ በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አደይ ፕሮግራም ድጋፍ የተደረገላቸው ሰባት የዶሮ እርባታ ማህበራት
 አሉት።

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ማህበራቱ በሥራቸው ያሰባሰቧቸው 94 አባላት አሏቸው፡፡ 

መንግሥት የዶሮ እርባታ ማህበራቱን ለማቋቋም 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር ብድርና የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቶ ወደ ሥራ በማስገባት ስኬታማ እንዲሆኑ እገዛ አድርጓል፡፡ 

ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በተዘጋጀው ችግኝ ማፍያ ጣቢያው ለአፈርና ውሃ ጥበቃ የሚያገለግሉ ችግኞች እየለሙ ነው። ከነዚህም ወይራ፣ ግራር፣ ቀርክሃና የአቮካዶ ችግኞች ይገኙበታል፡፡ 

የችግኝ ማፍላት ሥራው ለ120 ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የወርኅዊ ገቢ ባለቤት ሆነዋል፡፡ 
 
ሌላው በማዕከሉ እየተሰራ ያለው ቨርሚ ኮምፖስትን ማዘጋጀት ነው፡፡ ቨርሚ ኮምፖስቱ ከተለያዩ ተረፈ ምርቶች የሚዘጋጅ ሲሆን፣ ይህም የአፈርን ለምነትና ምርታማነት ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው።  

ቨርሚ ኮምፖስቱም ለማዕከሉ ችግኞች እንዲሁም በወረዳው አዳዲስ የችግኝ ጣቢያዎች የሚያቋቁሙ ወጣቶች ሥራ እንዲፈጥሩ ያገለግላል ይላል መረጃው፡፡

ማዕከሉ ችግኞች ከማፍላትና ከዶሮ እርባታ ሥራ ባሻገር ፍየል ማደለብ፣ ንብ ማነብ እንዲሁም የዓሳ እርባታ ስራን በማካተት በርካታ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት በመሥራት ላይ ነው፡፡ 


ኢኮኖሚሥራ ፈጠራግብርና

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!