እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:45:44 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ኢኮኖሚ

መንግሥት የነዳጅ አቅርቦትን የሚከታተል ልዩ ክፍል አቋቋመ

3 ደቂቃ ንባብ
መንግሥት የነዳጅ አቅርቦትን የሚከታተል ልዩ ክፍል አቋቋመ
መንግሥት የተፈጠረውን የአቅርቦት እጥረት ለመፍታትና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዳይገቱ ነዳጅን ከተጓዳኝ ገበያ እየገዛ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥በዚህም የዓለም የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት በሦስት እጥፍ ዋጋ ገዝቶ ለማቅረብ ተገዷል ብለዋል።
1 / 2

መንግሥት በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትና ዓለም አቀፍ ቀውስ ምክንያት በነዳጅ አቅርቦት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመቋቋም  የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን የሚከታተል፣ እርምጃ የሚወስድና የነዳጅ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች የሚለይ ልዩ ክፍል ማቋቋሙን አስታወቀ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄድ ያለው ያለው ጦርነትና አለመረጋጋት በአገሪቱ የነዳጅ ግብይትና አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

በዚህም ሳቢያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጦርነቱ በፊት የአንድ በርሜል ነጭ ናፍጣ ዋጋ 80 ዶላር የነበረ ሲሆን፥ አሁን 230 ዶላር መድረሱን ቤንዚንም ከ70 ወደ 150 ዶላር አሻቅቧል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር የነበራት የረጅም ጊዜ የነዳጅ ግብይት ውል በጦርነቱ ምክንያት አቅርቦት መስተጓጎሉንና አቅራቢዎቹ ምርቱን ማቅረብ እንደማይችሉ ማሳወቃቸውንም ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት በግዥ ሂደት ላይ የነበረ ከ180 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ነዳጅ አለመቅረቡን ጠቅሰዋል።

በጦርነቱና በተፈጠረው አለመረጋጋት  ምክንያትም በነጭ ናፍጣ ላይ የነበረው የቀን አቅርቦት ከ9 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሊትር ወደ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዝቅ ማለቱን በማሳያነት አቅርበዋል።

አገሮች ያጋጠማቸውን የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ተከትሎ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እቀባዎችን እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፥ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለው መርህ ግን ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ችግሩን በጋራ ለመሻገር መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግሥት የተፈጠረውን የአቅርቦት እጥረት ለመፍታትና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዳይገቱ ነዳጅን ከተጓዳኝ ገበያ እየገዛ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥በዚህም የዓለም የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት በሦስት እጥፍ ዋጋ ገዝቶ ለማቅረብ መገደዱን አስረድተዋል።

ምንም እንኳን የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምርም፣ መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ለመታደግ በአሁኑ ወቅት በነጭ ናፍጣ ላይ በአንድ ሊትር 95 ብር፣ በቤንዚን ላይ ደግሞ 42 ብር ድጎማ እያደረገ ይገኛል ነው ብለዋል።

መንግሥት እስካሁን 262 ቢሊዮን ብር ገደማ ድጎማ ማድረጉን ገልጸው፤ በየወሩም ከ15 እስከ 20 ቢሊዮን ብር ለድጎማ እየተመደበ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

መንግሥት የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በአገርና በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንዳያሳድርና በፍትሐዊነት ለመምራት ከዛሬ ጀምሮ የሚተገበር  የቅድሚያ አሰጣጥ ውሳኔ ማሳለፉን ይፋ አድርገዋል።

በዚህም መሠረት፥

1. ነዳጅ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች በማደያ የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው፣

2. ከፍተኛ አምራችና የኤክስፖርት ድርጅቶች በቀጥታ  ፣

3. ልዩ ትኩረት የሚሹ የመንግሥትና የግል ፕሮጀክቶች በቀጥታ፣

4. የገቢና ወጪ ንግድን ጨምሮ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች  ፣

5. ግብርናን የሚያዘምኑ ትራክተሮች፣

6. የከተማና እገር አቀፍ የብዙኃን ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ፣

7. እንዲሁም በናፍጣ የሚሰሩ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ነዳጅን በቅድሚያ እንዲያገኙ የሚያደርግ የቅድሚያ የነዳጅ አጠቃቀም አሠራር እንደሚተገበር ገልጸዋል።

ከዚህ ውጭ የሚደረግ የነዳጅ ስርጭት ተገቢ ባለመሆኑ እርምጃ ይወሰዳል ያሉት ሚኒስትር ካሳሁን፥ ይህንን ውሳኔ በአግባቡ ለማስፈጸም በቅንጅት እንደሚሠራም አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል መንግሥት የፌደራልና የክልል ተቋማትን ያካተተና ስርጭቱን 24/7 የሚከታተል የሁኔታዎች ልዩ የመከታተያ ክፍል ማቋቋሙን ይፋ አድርገዋል።

ከማዕከል ልዩ የመከታተያ ክፍሉን የነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭትና አጠቃቀምን የሚከታተል፣ ውሳኔዎችን የሚያቀርብና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን እንደሚለይ አስረድተዋል።

በነዳጅ ግብይትና አቅርቦት ዙሪያ ሕገ-ወጥ ድርጊት የፈጸሙ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ 658 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፣ ከ720 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ተይዞ ለመንግሥት ገቢ  መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ ከነዳጅ አቅርቦት ጋር የገጠመውን ችግር ለመወጣት የሚከተሉትን  ተግባራትን እንዲተገብር አሳስበዋል፦

1) ነዳጅን በቁጠባ እንዲጠቀም ፣

2) የታዳሽ ኃይል አማራጮችን የመጠቀም ስልትን መከተል፣

3) የእግር ጉዞ ባህልን ማጎልበት ፣

4) አላስፈላጊ የጉዞ ፕሮግራሞችን መሰረዝና ማቆም ፣

5) የሕዝብ ትራንስፖርትን መጠቀም ፣

6) በነዳጅ ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን በማጋለጥ ረገድ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ እንዲሠራም ተጠይቋል ።


የነዳጅ አቅርቦትየንግድና ቀጠናዊ ትሰስር ሚኒስቴር

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!