እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:47:50 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ

ሥልጠናው ዲጂታል የፈጠራ ሥራዎችን ለማሳደግ እያገዘ ነው

2 ደቂቃ ንባብ
ሥልጠናው ዲጂታል የፈጠራ ሥራዎችን ለማሳደግ እያገዘ ነው

ኢትዮጵያ ከዘመኑ ጋር ለመጓዝ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መሠረት ያደረገ ልማት እያካሄደች ነው።

በአገሪቱ ብዝኃ ኢኮኖሚ የልማትና የዕድገት አቅጣጫ ውስጥ ኢንፎርሜሽን፣ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ አንዱ ነው።

በአዲስ አበባና በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮሩ ዩኒቨርሲቲዎች ተቋቁመው ዘርፉን በሰው ኃይል በማሟላት አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ ናቸው።

የኢኖቪዬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በክልሎችና በከተሞች አስተዳደሮች የሚገኙት መሰል ተቋማትም የዘርፉን እንቅስቃሴ በማሳለጥ ሚናቸው የላቀ መሆኑ ይታመንበታል።

በኢትዮጵያ አምስት ሚሊዮን ወጣት ኮደሮች ለማሰልጠን ታቅዶ እስካሁን  3ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑት ሥልጠናው ማግኘታቸውም ተመላክቷል።

ወጣቱ ራሱንና አገሩን የዘመኑ ቴክኖሎጂ ከደረሰበት ደረጃ ለማድረስ በትጋት ሲንቀሳቀስ ማየትም የዕለት ተዕለት ክስተት ነው።ዓለም ከደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ቢቻልም ለመቅደም መንገዱ ይኸው ነውና።

በአገሪቱ የሚካሄደው የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ሥልጠና በተለይም ወጣቶች የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን እንደሚያሳድገው ይታወቃል።

በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች ስልጠናውን እየወሰዱ ከራሳቸው አልፈው፤ ለአገራቸው የዲጂታል ልማት ስትራቴጂ ትግበራ አሻራቸውን በማኖር ላይ ይገኛሉ።

የኢንፎርሜሽን፣ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ባለሙያዋ ጥሩ መልካም ስልጠናው በየትኛውም ሙያ የተሰማሩ ዜጎች ሥራቸውን ለማሻሻል ሚና እንዳለው ገልጻለች።

ተማሪ ባዩሽ ተስፋዬና ከደቡብ ሱዳን በነጻ ትምህርት ዕድል(ስኮላርሺፕ) ተጠቃሚ ላዱሊ ሞሪ የኢትዮ-ኮደርስ ሥልጠና ከዲጂታል ዘመን ጋር አብሮ ለመራመድ ክህሎትን ለማሳደግ ጠቀሜታ እንዳለው  ተናግረዋል።

በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ናኦል አንበሴ  በኢንስቲትዩቱ ተማሪዎችና ሠራተኞች ሥልጠናውን እንዲወስዱ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ያስረዳሉ።

የኢትዮ-ኮደርስ ሥልጠና ተጨማሪ ክህሎትን ለማጎልበት የሚረዳ በመሆኑ ዜጎች እድሉን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት መክረዋል ይላል ኢዜአ።

ሥልጠናው ዲጂታል የሥራ ፈጠራ ዕድሎችንና የፈጠራ ሥራዎችን በማስፋት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እያሳደገ መሆኑን የሚገልጹት  የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ ናቸው።

ሥልጠናው የዜጎችን ዲጂታል ክህሎት በማሳደግ የአኗኗር ዘይቤን የሚያሳልጡ ክህሎቶችን ለማጎልበት ያስችላል በማለትም ያብራራሉ።

በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ያላቸውን ክህሎት በማሳደግ ወደ ፈጠራ ስራዎች እንዲሸጋገሩ እገዛ ማድረጉን ገልጸው፣ይህም የአገሪቱን ተወዳዳሪነት በማሳደግ ወደ ዕውቀት መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው ሽግግር አስተዋጽኦ እንዳለው ብለዋል።

በትምህርት፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች በዲጂታል ሥርዓት እንዲታገዙ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አቶ ሰለሞን አስረድተዋል።







ኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂሳይንስና ቴክኖሎጂኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!