እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
05:11:30 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ሕግና ፍትሕ

በሕገወጥ ነዳጅ አስተላላፊዎች የሚደረገው ክትትል ተጠናክሯል-ግብረ ኃይሉ

3 ደቂቃ ንባብ
በሕገወጥ ነዳጅ አስተላላፊዎች የሚደረገው ክትትል ተጠናክሯል-ግብረ ኃይሉ
ግለሰብ በሸገር ከተማ ኮዬ ፈቼ ክፍለ ከተማ ቱሉ ዲምቱ ወረዳ ከሚገኝ አንድ የነዳጅ ማደያ ታንከር የተገለበጠ 46 ሺህሊትር ቤንዚን በማሽን በመታገዝ ወደ ተሽከርካሪ በመቅዳት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ይዞ ሲንቀሳቀስ ተይዟል።
1 / 2

የነዳጅ ጉዳይ የዓለማችን አሳሳቢና አንገብጋቢ ጉዳይ ከሆነ አንድ ወር አየተቆጠረ ነው።

አሜሪካና እሥራኤል በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የተስፋፋው ጦርነት ዋነኛ ዒላማዎች ከሆኑት መካከል ነዳጅ ማምረቻዎች፣ማከፋፈያዎችና ማስተላለፊያ መሥመሮች ይገኙበታል።

እንዲሁም የዓለም ንግድ አንድ አምስተኛ መተላለፊያ መሥመር የሆነው የሆርሙዝ ሰርጥ(ወሽመጥ) በባለቤትነት የምታሰተዳድረው ኢራን በመሥመሩ የሚተላለፉ መርከቦችን በመቆጣጠሯ ነዳጅ እንደልብ ማግኘት እንዳልተቻለ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ምንም እንኳን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን የኃይል ማመንጫዎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ አንወሰድም፤ከኢራን ጋር ድርድር ላይ ነን ቢሉም፤አብዛኛዎቹ ነዳጅ ሸማች አገሮች ገዝተው ለመጠቀም እየቻሉ አይደሉም።

በዚህም ሳቢያ አንዳንድ አገሮች ነዳጅን ለውሱን አገልግሎት ብቻ ለማዋል በቁጠባ ለመጠቀም ተገደዋል።በተለይ የግል ተሽከርካሪዎችን በየቀኑ በሙሉና ጎደሎ ቁጥር ከፋፍለው በማሰማራት፣የመንግሥት የሥራ ቀናትነ በመቀነስና ነዳጅ አልባ ትራንሰፖርትን በማበረታታት ይህንን ወቅት ለማለፍ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው እየተገለጸ ነው።

በነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ምክንያትም የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የተቋረጠባቸው አገሮች መታየታቸውን አንዳንድ መረጃዎች በዚህ ሣምንት አሳይተዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት ከውጭ ከፍተኛ ወጪ ተደርጎበትና  በውጭ ምንዛሪ የሚገባውን ነዳጅ ወቅቱን ባገናዘበ ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዲውል በተሰጠው መመሪያና ይሄንንም ተከትሎ የነዳጅ ስርጭትን የሚከታተልና የሚቆጣጠር ግብረ ኃይል በክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።

በአዲስ አበባ ከተማ የተቋቋመው ጥምር የፌደራል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ባደረገው ክትትል በሕገ-ወጥ መንገድ ነዳጅ ሲያዘዋወሩ የነበሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር አውሏል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መረጃ እንደሚያመለክተው የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 3 ኢት 92501 አሽከርካሪ የሆነ ግለሰብ በሸገር ከተማ ኮዬ ፈቼ ክፍለ ከተማ ቱሉ ዲምቱ ወረዳ ከሚገኝ አንድ የነዳጅ ማደያ ታንከር የተገለበጠ 46 ሺህሊትር ቤንዚን በማሽን በመታገዝ ወደ ተሽከርካሪ በመቅዳት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ይዞ ሲንቀሳቀስ ተይዟል።

ግብረ ኃይሉ ከኅብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ  ባደረገው ክትትል አሽከርካሪውን ከጫነው ነዳጅ ጋር በቁጥጥር ሥር እንዳዋለው አስታውቋል።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ለምቶ ሥራ ላይ በዋለው የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ በደረሰ መረጃ መነሻ በማድረግ በተደረገ ክትትል በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2 አዲስ አበባ 30279 ተሽከርካሪ አካል ላይ በሕገ-ወጥ መንገድ የነዳጅ ታንከር በማስገጠም ከተለያዬ ነዳጅ ማደያዎች ቤንዚን በመቅዳት በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያከፋፍል የነበረ ተጠርጣሪ ከአራት ግብረ አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ሥር ውሏል።

የተጠርጣሪውና ግብረ አበሮቹ በንፋስ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝም  መረጃው ያሳያል።

በቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰብ በሕገ-ወጥ መንገድ የቀዳውን ነዳጅ ወረዳ  አንድ ጀሞ አካባቢ ከሚገኝ መኖሪያ ግቢ ለማራገፍ ሲመጣ እጅ ከፍንጅ መያዙንም የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ያስረዳል።

በግቢ ውስጥ እያንዳንዳቸው 200 ሊትር ነዳጅ የያዙ 12ና ሌሎች በርካታ በርሜሎች የተገኙ ሲሆን፣ በሕገ ወጥ ድርጊት የተገኘው አሽከርካሪ እንቁላል አከፋፋይ በመመሰል ወንጀሉን ሲፈፅም እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ግብረ ኃይሉ ከክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያና ከክፍለ ከተማው ንግድና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት በመቀናጀት የተያዘው ነዳጅ በሕግ አግባብ ወደ ሌላ ማደያ እንዲገለበጥ ተደርጎ ከሽያጩ የሚገኘው ገንዘብ በዝግ አካውንት ለመንግሥት መሆኑ ጠቅላይ መምሪያው አስረድቷል።

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጥቶበት ወደ አገር ውስጥ የሚገባን የነዳጅ ምርት በሕገ ወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩ ነዳጅ የሚደብቁና መሠል የወንጀል ድርጊት ውስጥ በሚገቡ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ የሚወስደውን ሕጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም በመረጃው ተመላክቷል።


ሕገ ወጥ ድርጊትየነዳጅ ቁጥጥር

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!