
መንግሥት በዚህ ሣምንት መግቢያ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በተከሰተው ግጭት የነዳጅ እጥረት በመከሰቱ ነዳጅን በቁጠባና ለተወሰኑ ቁልፍ ጉዳዮች ቅድሚያ እንዲሰጥ ወስኗል።
እንዲሁም በሕገ ወጥ የሚንቀሳቀስ ነዳጅ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ መመሪያ አስተላልፏል።
መመሪያውን ተከትሎ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች መመሪያውን ለማስፈጸም እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምረዋል።
ከነዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሕገ ወጥ ከከተማው ሊወጣ የነበረ ስድስት በርሜል ነዳጅ ከነ ተጠርጣሪዎቹ ይዟል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ በተደረገ እንቅስቃሴ ዳቤ ክፍለ ከተማ በሕገ ወጥ መንገድ ከነዳጅ ማደያ የተቀዳ ከ4 ሺህ300 ሊትር በላይ ናፍጣ ሲጓጓዝ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የከተማው ፖሊስ አስታውቋል።
የከተማው አስተዳደር ፖሊስ ዋና መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ሸዋዬ ደቻሣ እንደገለጹት በከተማው ነዳጅ ማደያ በ21 በርሜሎች ተጭኖ በሌሊት ሲጓጓዝ ተይዟል።
በሕገ ወጥ ከከተማው ሊወጣ የነበረው ናፍጣ በክፍለ ከተማወ ሰሎቄ ደንጐሬ ወረዳ ከሚገኝ ነዳጅ ማደያ በሕገ ወጥ መንገድ የተቀዳ መሆኑንም አስረድተዋል።
የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ3A 19682 አዲስ አበባ በሆነ ተሽከርካሪ የተጫነው ናፍጣ በቁጥጥር ሥር የዋለው በሦስት ግለሰቦችና ለጊዜው ባልተያዘው አሽከርካሪ አማካይነት ነው።
በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል የነዳጅ ማደያ ሥራ አስኪያጅ፣ በድለላ ስራ ላይ የተሰማራ ግለሰብና ነዳጁን ሲያጓጉዝ የነበረ ተሽከርካሪ ረዳት በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ሲሆን፣ የተሽከርካሪው አሽከርካሪ ደግሞ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን አዛዡ ተናግረዋል።
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!