እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:47:07 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ማህበራዊ

በእናቶችና ሕፃናት ክብካቤና ተያያዥ ጉዳዮች ያተኮረ ጥናት ይካሄዳል

1 ደቂቃ ንባብ
በእናቶችና ሕፃናት ክብካቤና ተያያዥ ጉዳዮች ያተኮረ ጥናት ይካሄዳል
ጥናቱ የሚሰበስባቸው መስኮች መረጃዎች የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መሠረት እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡
1 / 3

ጤና ሚኒስቴር በእናቶችና ሕፃናት ክብካቤ፣ ቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት አሰጣጥ ክትባት ላይ ትኩረት ያደረገ የዳሰሳ ጥናት ሊያካሄድ መሆኑን ገለጸ፡፡

ሚኒስቴሩ ከአዲስ አበባ ከጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ጥናቱን ያካሂዳል፡፡ 

የዳሰሳ ጥናቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በእናቶችና ሕፃናት ጤና አጠባበቅ ዙሪያ  ፋይዳ ያለው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የመስክ ሥራ መጀመሩም ይፋ ተደርጓል፡፡

ጥናቱ የሚሰበስባቸው መስኮች መረጃዎች የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መሠረት እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንደገለጹት፤ መንግስት መረጃን መሠረት ያደረገ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓትን ለመገንባት በሰጠው ትኩረት በእናቶችና ሕፃናት ላይ ይደርስ የነበረውን የሞት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል።

ይህ ውጤት ሊመዘገብ የቻለውም ከለውጡ ወዲህ የጤና ተቋማትን በማስፋፋት፣ ግብዓቶችን በማሟላት እናቶች በቅድመና ድህረ ወሊድ ወቅት የሕክምና ክትትል እንዲያደርጉ ግንዛቤ በመፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን የሚካሄደው የዳሰሳ ጥናት በተለይም በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነት፣ በእናቶችና ሕፃናት የጤና ክብካቤ ጥራት እንዲሁም በክትባት ሽፋን ዙሪያ ያለውን ተጨባጭ መረጃ ለማወቅና ለቀጣይ የፖሊሲ ውሳኔዎች እንደ ግብዓት ለመጠቀም ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር ሙሉጌታ ታምሬ በበኩላቸው፤ ጥናቱ ሁሉንም የአገሪቱ ክልሎች እንደሚያካትት አስታውቀዋል። 

የኢትዮጵያ አፈጻጸም ክትትል ትግበራ ጥናት ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀ መረጃን በማቅረብ የጤናውን ዘርፍ ውጤታማነት ለማረጋገጥና በዘርፉ የልህቀት ማዕከል ለመገንባት ያግዛል ብለዋል።

በዚሁ የምርምር ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የጤና የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡


 

እናቶችና ሕፃናት ክብካቤጤናቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!