እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:45:44 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ኢኮኖሚ

በኦሮሚያ ክልል 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ቀረበ

2 ደቂቃ ንባብ
በኦሮሚያ ክልል 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ቀረበ
ለዘንድሮው የበልግና መኽር እርሻ የሚውል እስካሁን 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በዩኒየኖችና በኀብረት ሥራ ማህበራት ጋር ደርሷል
1 / 2
በኦሮሚያ ክልል ለዘንድሮው የበልግና መኽር እርሻ 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ዩኒየኖችና በኅብረት ሥራ ማህበራት ጋር መድረሱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ሙስጠፋ ሁሴን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ለክልሉ አርሶ አደሮች ለበልግና ለመኽር አዝመራ የሚውል የግብዓት አቅርቦት በተቋማ በኩል ብቻ እንደሚሰራጭ ገልጸዋል።

በክልሉ በዘንድሮው የልማት ወቅት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከአርሶ አደሮች፣ ከልማት ጣቢያ ባለሙያዎችና ከዘርፉ አመራሮች ጋር  ውይይት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱንም ጠቁመዋል።

በዚህም መሠረት የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እየቀረበ መሆኑንና ልማቱም በኩታ ገጠም አሰራርና ቴክኖሎጂን በመጠቀም እንደሚከናወን ዳይክተሩ አስረድተዋል።

ለዘንድሮው የበልግና መኽር እርሻ  የሚውል እስካሁን 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በዩኒየኖችና በኀብረት ሥራ ማህበራት ጋር ደርሷል ማለታቸው ኢዜአ ዘግቧል።

በበልግ አዝመራው በክልሉ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሚለማ ሲሆን፣ ለዚህም 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር መዘጋጀቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ከበልግ አዝመራው 46 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ግብ ተቀምጦ ወደ ሥራ መገባቱን የጠቀሱት አቶ ሙስጠፋ፤ ድርቅን መቋቋም የሚችሉና ቶሎ የሚደርሱ  የማሾ፣ በቆሎ፣ ቦሎቄ፣ ማሽላ፣ ስንዴ፣ ገብስና አተር ሰብሎች በስፋት እንደሚለሙ ገልጸዋል።

የበልግ አብቃይ በሆኑት በሁለቱ የሐረርጌና ሁለቱ የባሌ ዞኖች፣ ጉጂ፣ ምሥራቅ ቦረና፣ አርሲና ምሥራቅ ሸዋን ጨምሮ በዘጠኝ ዞኖች ልማቱ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በመኸር አዝመራም በአጠቃላይ 11 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት የታቀደ ሲሆን፣ ለዚህም 10 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዷል ብለዋል።

በተጨማሪም ምርታማነትን ለመጨመር ለአሲዳማ አካባቢዎች 400 ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተናግረዋል ዳይሬክተሩ።

የብርዕ፣ የአገዳ፣ የቅባትና የጥራጥሬ ሰብሎችን ጨምሮ 23 የሰብል አይነቶች በክላስተር አሰራር እንደሚመረቱም ገልጸዋል።


ማዳበሪያግብርና

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!