እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:47:18 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ማህበራዊ

በኦሮሚያ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ይስፋፋል-ቢሮው

2 ደቂቃ ንባብ
በኦሮሚያ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ይስፋፋል-ቢሮው
በኦሮሚያ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ የአገልግሎት ፍትሃዊነት፣ የተገልጋይ ምልልስ መቀነስ፣ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰራ ተገልጿል;

በኦሮሚያ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ገለጸ።

የክልሉ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ከክልሉ ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ተደራሽ ማድረግ፣ በቴክኖሎጂና በሰለጠነ የሰው ኃይል ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።

የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ኮከቤ ዲዳ አገልግሎቱ በክልሉ አምስት ከተሞች ተግባራዊ መደረጉን አንስተው÷ በዚህም የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተቻለ ነው ብለዋል።

አገልግሎቱን በሁሉም አካባቢዎች አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው÷ ኀብረተሰቡ የሚያነሳባቸው የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ማስቻል ትኩረት እንደሚፈልግ  ተናግረዋል።

የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በተመለከተ 7 ሺህ 800 በላይ የተገልጋዮች ሐሳብ የሰበሰበው የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ÷ የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ገልጿል።

የአገልግሎት ፍትሃዊነት፣ የተገልጋይ ምልልስ መቀነስ፣ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰራ ተገልጿል።

በተጨማሪም አገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ከማድረግ አንፃር በተገልጋዩ ዘንድ ቅሬታ እንደሚነሳ አንስቷል።

ከተገልጋዮች የተነሳውን ሐሳብ መነሻ በማድረግ ምላሽ የሰጡት የቢሮ ኃላፊዋ ኮከቤ ዲዳ÷ ማዕከላቱን ተደራሽና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ እንዲሁም ከደላላ ነፃ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይም ተገልጋዩ ቅሬታ የሚያነሳባቸው ጉዳዮች ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብዙ ችግሮችን ለመፍታት እያስቻለ እንደሆነና በተለይም ተቋማት በመቀናጀት መስራት እንደሚጠበቅባቸው በመድረኩ ተነስቷል።

በአዲስ አበባ የተጀመረው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት እየተስፋፋ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ኢትዮጵያ የመሶብ አንድ ማዕከል ልምድ የቀሰመቸው ከአዘርባጃን መሆኑ ይታወቃል፡፡

ሲቪል ሰርቪስየመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትኦሮሚያ ክልል

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!