
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የአገሪቱን የሳይበር ምህዳር አስተማማኝ ለማድረግና የዘርፉን የሰው ኃይል ለማፍራት የሚሰራ ተቋም ነው፡፡
በዚህም ባለፉት ዓመታት በሦስት የአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይበር ደህንነት ክለቦች እንዲቋቋሙ አድርጓል።
ከሐረማያ፣ ከዓርባ ምንጭና ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች በመቀጠል የጀመረውን ጥረት በመቀጠል ዛሬ በምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኝ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ክለብ አቋቁሟል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሳይበር ክለብ በይፋ ተመሥርቷል።
በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተካሄደው የምሥረታ መርሐ-ግብር ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የኢመደአ የሥራ ኃላፊዎችና ተማሪዎች ተገኝተዋል።
የኢንስቲትዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ኢንጂነር ኤፍሬም ዋቅጅራ በዩኒቨርሲቲው የተመሰረተው የሳይበር ክለብ የአገሪቱን የዲጂታል ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ ልዩና ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር መሐመድ ሙንታዝ (ዶ/ር)በበኩላቸው በአገሪቱ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ በመከናወን ላይ የሚገኙት ዐበይት ተግባራትን አስተዋውቀዋል።
ከነዚህም የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ሥልጠና ኢኒሼቲቭንና የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይን መሠረት ያደረገ ገለጻ አድርገዋል።
የዲጂታል ቴክኖሎጂው የሰው ልጆችን በማቅለል ከሚጫወተው አዎንታዊ ባሻገር፤የሳይበር ስጋቶች (Threats on the Cyberspace) እያደረሰ ባለው ጥፋት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥተዋል።
ክለቡ ተማሪዎች በንድፈ-ሐሳብ የሚቀስሙትን ዕውቀት በተግባራዊ ክህሎት እንዲያዳብሩ ሚና እንደሚጫወትም ዳይሬክተሩ እምነታቸውን ገልጸዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ባህል ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ቢንያም ማስረሻ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ተማሪዎች ክለቡን በመቀላቀል ራሳቸውንና አካባቢያቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ አሳስበዋል።
የነገዋን ኢትዮጵያ የሳይበር ምህዳር የሚጠብቁ ብቁ ባለሙያዎች ሆነው ወደ ሥራው ዓለም እንዲቀላቀሉም ጠቁመዋል።
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!