
በአማራጮቸ ኤክስፖርት ኢምፖርት (አፍሪኤግዚም)ባንክ በባህረ ሰላጤው አገሮች በተከሰተው ቀውስ ኢኮኖሚያቸው ለተጎዳ የአፍሪካና ካሪቢያን አገሮች መታደጊያ 10 ቢሊዮን ዶላር መደበ።
ባንኩ ለአገሮቹ ኢኮኖሚ ማገገሚያ የሚሆነውን ገንዘብ እንዲለቀቅ የወሰነው ዛሬ የባነኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ባሳለፈው መሠረት ነው።
ባንኩ ከአንድ ወር በፊት በተቀሰቀሰው በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በተቀሰቀሰው ጦርነት ኢኮኖሚያቸው ለተጎዱት የፈቀደው ብድር ለፋይናንስ ተቋማትና ኮርፖሬቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል።
ጦርነቱ በነዳጅ፣በፈሳሽ ተፈጥሮ ጋዝ፣ማዳበሪያ አምራች በሆኑ አገሮች ላይ በመከሰቱና የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ ከባድ ጉዳት አድርሷል።
የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በጦርነቱ ሳቢያ ከነዳጅ ከሚያገኙት ባሻገር፤በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ዘርፎች ያላቸው ገቢ ቀንሶባቸዋል።
በፕሮግራሙ የሚጠቀሙ አገሮች የተፈደው ብድር በዋነኝነት ነዳጅ፣ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ፣ምግብ፣መድኃኒት አስገቢ አገሮች በአጭር ጊዜ በሚደርስ ብድር በማቅረብ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ብሏል ባንኩ።
በተጨማሪም የአፍሪካ የኢነርጂና የማዕድን ዘርፎች አምራቾች አጋጣሚውን ተጠቅመው ምርቶቻቸውን በአማራጭ መሥመሮች ለገበያ ለማቅረብ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ገልጿል።
እንዲሁም ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ምርቶችን ለገበያ ለማቅረብ የፋይናንስ፣የመሥሪያ ካፒታልና ተጨማሪ ድጋፍ ይሆናቸዋል ሲልም አብራርቷል።
ፕሮግራሙ ኢኮኖሚያቸው በቱሪዝምና አቪዬሸን ዘርፎች ጥገኛ ለሆኑ አገሮች መታደጊያ የሚሆን የአጭር ጊዜ ማካተቱንም ባንኩ ያሰራጨው መረጃ ያመለክታል።
ፕሮግራሙ በአፍሪካና በካሪቢያን የሚገኙ የባንኩን አባል አገሮች ኢኮኖሚ ከመካከለኛ እስከ ረጅም ጊዜ በሚዘልቅ የችግር መቋቋሚያ በመገንባት አቅም ይፈጥርላቸዋል ተብሎም ይታሰባል።በዚህም በተለይ ኢነርጂ አምራችና ሻጭ አገሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ የኢነርጂ ፣የወደብና የሎጀስቲክስ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ግንባታ አፋጥኖ አገልግሎት ለማስጀመር ያስችላል ተብሎ ተስፋ መደረጉን አስታውቋል።
የአፍሪካ ኤክስፖርት ኢምፖርት (አፍሪኤግዚም)ባንክ ፕሬዚዳንትና የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ጆርጅ ኦሎምቤ(ዶ/ር)በሰጡት አስተያየት ባንኩ በጦርነቱ ሳቢያ ችግር ውስጥ የወደቁ አገሮች ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ፕሮግራሙን መዘርጋቱን ገልጸው፣በዚህም ችግሩን ተቋቁመው በመውጣት ኢኮኖሚያቸው እንዲያገመግም ይረዳቸዋል ብዬ አስባለሁ ብለዋል።
ባንኩ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን፣ከአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን፣ ከአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ከካሪቢያን አገሮች ድርጅት ችግሮቹን ለማቋቋም ቀጣናዊ ትብብር በኢኮኖሚ፣በንግድ ማሳለጥና በአቅርቦት ሰንሰለት አማራጮች ላይ እየተነጋገረ መሆኑንም ገልጿል።
ከተመሠረተ 30 ዓመታት ያስቆጠረው ባንክ በዓለማችን ታላላቅ ቀውሶች ሲከሰቱ የመታደጊያ ፕሮግራሞችን በመዘርጋት አገሮችን ሲታደግ መቆየቱንም አስታውሷል።
አሜሪካና አሥራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ፤ኢራንም በአሥራኤልና የአሜሪካ አጋሮች በምትላቸው የመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች ሚሳኤሎችንን ድሮኖችን መተኮስ ከጀመረች 40 ቀናት ተቆጥረዋል።
ጦርነቱን ተከትሎ ኢራን የዓለም 20 በመቶ ያህል የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቷ በተለይ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚገዛውን ነዳጅ ለማስገባት ባለመቻሉ በርካታ አገሮች ችግር ውስጥ ወድቀዋል።
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!