
ግንቦት 24ቀን 2018 በኢትዮጵያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድበት ቀን ነው።
ለዘንድሮው ምርጫ እስካሁን በዋነኝነት የተከናወነው የፖለቲካ ድርጅቶችና የግል ዕጩዎች ምዝገባ ሲሆን፤ከየካቲት 28 ቀን ጀምሮ ደግሞ የምርጫው ዋነኛ ተሳታፊዎች የመራጮች ምዝገባ በመካሄድ ላይ ነው።
ላለፉት ስድስት ሣምንታት ያህል በመገናኛ ብዙኃን የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ማኒፌስቶአቸውንና አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውን ያስተዋወቁበትና ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር የተከራከሩባቸው መድረኮች በመደረግ ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ያዘጋጀው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክር ትናንት ማካሄድ ጀምሯል።
ቦርዱ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባዘጋጀው የመጀመሪያው የክርክር መድረክ ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት(ሰላም)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ፓርቲ፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነትና ብልፅግና ፓርቲ ተሳትፈዋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ መድረኩ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭና ፕሮግራሞቻቸውን ነጻ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለሕዝብ የሚያደርሱበት እንደሆነ አስታውቀዋል።
መድረኩ መራጮች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አማራጭ ሃሳቦች በማጤን በዕውቀትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ድምፅ እንዲሰጥ ለማድረግ እንደሚያስችል አመላክተዋል።
ምርጫ ክርክር የዝግጅት ምዕራፍ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጫቸውን ለሕዝብ የሚያደርሱባቸው ርዕሰ ጉዳዮች በገለልተኛ ባለሙያዎች ጥናት መካሄዱንም በመግለጽ።
በተጨማሪም በክሩክሩ ወቅት የሚቀርቡ አኀዛዊ መረጃዎችና ሐሳቦች ትክክለኝነት የሚመዝኑና የሚያጣሩ ባለሙያዎች እንዲካተቱ መደረጉንም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
መድረኩም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ተሳትፎ ለዲሞክራሲ ምኅዳር መጎልበት ይረዳል ብለዋል።
መድረኩ መራጮች የድምፅ መስጫ ካርድ እንዲወስዱ ከፍተኛ መነቃቃት እንደሚፈጥር ሰብሳቢዋ እምነታቸውን ገልጸዋል።
ዛሬ ከዘንድሮው ምርጫ ጋር በተያያዘ ሌላ ዐቢይ ተግባር የተከነወበት ቀን ሆኗል፡፡
ቦርዱ በቅድመ ምርጫ ተግባራቱ ከሚያከናውናቸው በርካታ ሥራዎች ውስጥ “በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 44 (3) እና “በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ ዐዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 7 እንዲሁም “በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በመገናኛ ብዙኃን ዐዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 71 (4) እና (5) በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎችን “የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም” በጋራ ተፈጻሚ ማድረግ ተጠቃሽ ነው፡፡
በዚህም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ የአየር ሰዓት ድልድል የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዎች ያለምንም ክፍያ የሚጠቀሙበትን የድልድል አሰራር ይፋ አድርገዋል።
ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 19 ቀን 2018 ድረስ በሚቆየው ድልድል፤የፖለቲካ ፓርቲዎች የተደለደለላቸውን የአየር ሰዓትና የጋዜጣ ዓምዶች ከቅዳሜ፣ እሁድና የበዓላት ቀናት ውጭ እንደሚጠቀሙበት ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ባዘጋጀው ቀመር መሠረት ድልድሉ "አካታችነትን" ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፣ አከፋፈሉም በሚከተለው ስሌት ተከናውኗል፦
40% ለሁሉም ፓርቲዎች እኩል፤
25% ባቀረቧቸው ዕጩዎች ብዛት፤
15% በአካል ጉዳተኛ ዕጩዎች ብዛት፤
15% በሴት ዕጩዎች ብዛት፤
5% በሴት አካል ጉዳተኛ ዕጩዎች ብዛት ተሰልቶ ተደልድሏል፡፡
በዚህም መሠረት ለ47 የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች በሬዲዮ 782ነጥብ 5 ሰዓታት፣ በቴሌቪዥን 513 ሰዓታት እንዲሁም 576 የጋዜጣ ዓምዶች ተመድብውላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ እንዳስረዱት፤ ድልድሉን ለማውጣት ለረዥም ጊዜ ጥንቃቄ የተሞላበት ዝግጅት አድርጓል፡፡
በተለይም ቴክኖሎጂን በመጠቀም የቀን፣ የሰዓትና የቋንቋ ዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ ግልጽና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መከናወኑንም ገልጸዋል።
ድልድሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውንና ፖሊሲዎቻቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ የግል ዕጩዎችም አማራጭ ሐሳቦቻቸውን እንዲያጋሩና የምርጫ ቅስቀሳ እንዲያደርጉና ከመራጩ ጋር እንዲተዋወቁ ዕድል እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡
ይህም ለፓርቲያቸው ብቻ ሳይሆን፤ሕዝቡ የመራጮች ካርድ እንዲያወጣ መነሳሳትን እንደሚፈጥርና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲሰጥ ያግዛል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኃይማኖት ዘለቀ ነፃ የአየር ሰዓት ድልድል በ50 መገናኛ ብዙኃን የተደለደለ ሲሆን፤ ድልድሉ የምርጫውን ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንደተከናወነ አስረድተዋል።
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተደለደለው ነፃ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ ዓምዶች ለስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከተመደበው የ10 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል፡፡
ድልድሉ በ24 የግልና የሕዝብ ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ በ20የሕዝብና የንግድ ቴሌቪዥን ጣቢያዎችና በስድስት የሕዝብ ጋዜጦች ተፈጻሚ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
ፍትሐዊና ግልጽ የውድድር ሜዳ ለመፍጠር ያለመው ድልድል በኤሌክትሮኒክስ ጣቢያዎቹና በሥራቸው ባሉት ቻናሎችና በቋንቋዎች ሲታሰብ በ66 ቻናሎች እንደሚሆን ዋና ዳይሬክተሯ አብራርተዋል፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎች የአየር ሰዓቱን ሲጠቀሙ ሕገ መንግሥቱን፣ የምርጫ ሥነ ምግባር ዓዋጁንና ሌሎች ሕጎችን እንዲሁም የማህበረሰቡን ባህልና እሴትን በጠበቀ መልኩ እንዲጠቀሙብት አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ባለፈው ምርጫ ወቅት በሬዲዮ ከተሰጠው ሰዓት ጥቅም ላይ የዋለው 53 በመቶው ብቻ እንደነበር በማስታወስ፤ አሁን የተደረገውን የ10 በመቶ ጭማሪ ፓርቲዎች በኃላፊነት ስሜት ለሕዝብ ተደራሽ ለመሆን እንዲጠቀሙበት መክረዋል።
የዘንድሮው ምርጫ ቅስቀሳ ግንቦት 19 ቀን የሚያበቃ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ አራት ቀናት ደግሞ ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት መራጩ ሕዝብ የሚመክርባቸው "የአርምሞ ቀናት "ይሆናሉ ተብሏል።
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!