እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
03:39:24 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ማህበራዊ

ትንሣኤ-ከዐቢይ ፆም ፍቺ በላይ ነው

8 ደቂቃ ንባብ
ትንሣኤ-ከዐቢይ ፆም ፍቺ በላይ ነው
በትንሣኤ በዓል የሐይማኖት አባቶች ቡራኬና የመልካም ምኞት መግለጫዎች የበዓሉ አካል ሆነው በመገናኛ ብዙኃን ይተላለፋሉ።
ዛሬ ትንሣኤ ነው።ትንሣኤ ማለት ደግሞ በዓለማዊ ትርጉሙም ዳግም መፈጠር ፤በአዲስነት መከሰት ማለት ነው።
ያው ከመንፈሳዊ ወይም ሐይማኖታሚ ትርጉሙ እምብዛም ባልራቀ ትርጉሙ።

ለማንኛውም ዕለቱን ወይም በዓሉን የሚመለከተውን ጉዳይ ኋላ እንመለስበታለን።

ከዚያ በፊት ከትንሣኤ በፊት ያለውን ታላቁን የጾም ወቅትና ተያያዥ ጉዳዮችን እያነሳን እንጨዋወት።

ለማንኛውም እንኳን ለ2018 የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ!!! 

በመሠረቱ ጾም ማለት ሁሉንም ሕዋሳት ከኃጢዓት መከልከል፣ለተወሰነ ጊዜ ምግብ ከመብላት፣ ውሃ ከመጠጣት መታቀብ ወይም ለተወሰኑ ወራት ከሥጋ ፣ከወተት፣ ከቅቤ፣ ከእንቁላል  በአጠቃላይ ከእንሰሳት ውጤት መከልከል ነው።

ከምግብና መጠጥ  እቀባው ባሻገር ጾም የሥጋ ምኞትን የምታጠፋ የነፍስን ቁስል የምታደርቅ፣ለጎልማሶችም ጸጥታንና እርጋታን የምታስተምር ከእንሰሳዊ ግብር ጠባይ የምትከለክልና ሰው መላእክትን መስሎ የሚኖርባት ሥርዓት መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

እግዚአብሔር የጾምን ሥርዓት የደነገገው አዳምን በፈጠረበት ወቅት ነው ፡፡አዳምን እፀ በለስን አትብላ ባለው  ጊዜ። እግዚአብሔር የሰጠው ይህን ትዕዛዝ  አዳምና ሔዋን ይህን በመሻር እጸ በለስን በልተው ምን እንደደረሰባቸው የሚታወቅ ነው፡፡
የበዓሉን መነሻና መዳረሻ የሆነውን ዐቢይ ፆም ከመመልከታችን በፊት በተለይየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለጾም  ያወጣችውን ሥርዓትና ደንብ ማወቁ ጠቃሚ ነው።ቤተ ክርስቲያኗ በዓመት ውስጥ ሰባት የዓዋጅ አጽዋማት እንዳሉና ማንኛውም ክርስቲያን እነዚህን አጽዋማት እንዲጾሙ ታዛለች። እነዚህም፦
ጾመ ሐዋርያት
ጾመ ስብከት (ጾመ ነብያት)
ጸመ ፍልሰታ
ጾመ ድኅነት
ጾም ነነዌ
ጾመ ገሃድ
ዐቢይ ጾም ናቸው።
ከነዚህ አጽዋማት ውስጥ ከበዓሉ ጋር የቅርብ  ግንኙነት ያለውን በጾሙ ማጠቃለያ የምናከብረውን ዐቢይ ጾምን እንመለከታለን ።

ዐቢይ ጾም ማለት ምን ማለት ነው?
በመጀመሪያ ‹‹ዐቢይ›› የሚለው ቃል ‹‹አበየ›› ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ትርጓሜውም ‹‹ከፍ አለ›› ማለት ነው፡፡

ዐቢይ ጾም የተባለው  በሦስት ዐበይት ምክንያቶች ነው፦
አንደኛው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የጾመው በመሆኑ ነው።
ሁለተኛው ምክንያት የጾሙ ርዝማኔ ከሌሎች አጽዋማት የሚበልጥ በመሆኑ ነው።ዐቢይ ጾም ለ55 ቀናት ስለሚጾም ማለት ነው።
ሦስተኛው ምክንያት ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች እንዲሁም ደግሞ ሶስቱ ርዕሰ ኃጢአትየሚባሉት ትዕቢት፣ስስት ፍቅረ ነዋይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ድል የተመቱበት በመሆኑ ነው የሐይማኖቱ አባቶች እንደሚሉት።

ዐቢይ ጾም ሌሎች ስያሜዎችም አሉት።ከነዚህም ጥቂቶቹን ቀጥለን እንመልከታቸው፦
ጾመ ሁዳዴ፡- ሁዳድ ማለት ሠፊ (ትልቅ) የእርሻ ቦታ ማለት ነው፡፡ ይህም ጾም ደግሞ በቀኑ ብዛት ረጅም በመሆኑ የሁዳዴ ጾም ይባላል።
የካሳ ጾም፡- እንዲህ የተባለበት ምክንያቱ ደግሞ አዳምና ሔዋን በዲያቢሎስ ግዞት እያሉ ክርስቶስ ደሙን በመክፈል ነጻ ስላውጣቸው የካሳ ጾም ተብሏል።
የድል ጾም ፡-ይህም ደግሞ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ጾም ሰይጣንን ድል ያደረገበት በመሆኑ የድል ጾም ተብሎም ይጠራል፡፡
ጾም አስተምህሮ፡- ይህ ጾም ‹‹ጾም አስተምህሮ›› የተባለበት ምክንያት ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  የሰው ልጆችን ለማስተማር የጾመው የተሰጠው ስያሜ ነው፡፡

የዐቢይ ጾም ሣምንታት
በዐቢይ ጾም ሰባት ቅዳሜዎችና ስምንት እሁዶች ይውላሉ።
ስምንቱ እሁዶች የተለያየ ስያሜ አላቸው፡፡ ስያሜቸውንም የሰጣቸው የዜማው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡
የመጀመሪያው ሣምንት  ዘወረደ፣
ሁለተኛው ሣምንት  ቅድስት፣
ሦስተኛው ሣምንት ምኩራብ፣
አራተኛው ሣምንት ደብረዘይት፣
አምስተኛው ሣምንት ገብረ ሔር፣
ስድስተኛው  ሣምንት ኒቆዲሞስ፣
ሰባተኛው  ሣምንት መጻጉዕ፣
ስምንተኛው  ሣምንት  ሆሳዕና ይባላሉ።

ከሣምንታቱ ሁሉ የመጨረሻው የሆነውን ሆሳዕና በአርያምንና በተከታታይ ያሉትን ቀናት ከእምነቱ ጋር አስተሳሰረን በጥቂቱ እንቃኛቸው።

ሆሳዕና በአርያም
ሆሳዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ተብሎ የሚጠራው ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መግቢያ ዋዜማ ነው።

በዚህ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ‘ሆሣዕና በአርያም’’ ‘ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት’’ ‘ዕለተ ሆሣዕናሁ አርአየ… ‘ ወዘተ. በማለት ሆሣዕና የሚለውን ቃል ቅዱስ ያሬድና ሌሎችም አባቶች በየቦታው እየጠቀሱና እየተዘመረለት በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ እየተረከ ስለሚዘምር በጌትነትና በክብር በውዳሴና ቅዳሴ ሆሣዕና በአርአያም እየተባለ በሽማግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮችም ልሳን ሳይቀር እየተመሰገነ ወደ ኢየሩሳሌም በከብር ሲገባ ለሰጣቸው ለተቀደሰ ሰላሙና ፍቅሩ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ ነው።

የሆሣዕና በዓል በቤተክርስቲያን ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ ሕዝቡ ፀበርት ወይም ዘንባባ በመያዝ ‘ቡርክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር – በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረክ ነው።’’ መዝ.117፣26 በማለት ስለተቀበሉት ይህን በማሰብና በማድረግ ቤተክርስቲያናችን ዘንባባ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ታድላለች። በቤተክርስቲያን በአራቱም ማዕዘናት ይህን በዓል የሚመለከቱ የቅዱስ ማቴዎስ (ማቴ. 21፣1-17)፤ የቅዱስ ማርቆስ፣(ማር.11፣1-10)፤ የቅዱስ ሉቃስና (ሉቃ.19፣29-38)፤ የቅዱስ ዮሐንስ (ዮሐ.12፣12-15) ወንጌላት ይነበባሉ ።

ሰሙነ ሕማማትና ሰቅለት

ሰሙነ ሕማማት ተብሎ የሚጠራው ወቅት ከዐቢይ ጾም መጨረሻ ከሆሣዕና ዋዜማ ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ባሉት ቀናት ውስጥ ያለው ሳምንት ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ይህንን ወቅት አስመልክቶ  በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ‹‹ውእቱ ነሥአ ደዌነ ወጾረ ሕማመነ፤ እርሱ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፤›› በማለት የነገረ ሕማማቱን ምሥጢር አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ በዚህም መሠረት በኋለኛው ዘመን እግዚአብሔር ወልድ ስለኛ ስለ ሰው ልጆች ድኅነት ሲል ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋም ነፍስ ነሥቶ በፈቃዱ ሰው ሆኖ በፈቃዱ መከራ መስቀልን ተቀበለ፡፡ በመስቀሉም ላይ ሳለ በፈቃዱ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ፡፡

በዚህ ሳምንት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ በሙሉ ያደረገውን ትድግና ቅዱሳት መጻሕፍት በተለይም ግብረ ሕማማት የተባለው  ነገረ ሕማማቱን መከራውና መሰቀሉን በሰፊው ይነገርበታል።

 የስቅለት (crucifixion) ቀን እጅግ ልዩ ናት፡፡ የስቅለት ዕለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ “የድኅነት ቀን” ወይም ‹‹መልካም ዓርብ›› ይባላል፡፡ ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡ ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት (ማቴ. 27፥1-57)፡፡ ይህን አጥተቀል የሚሉት ነገር ሳይኖራቸው ጌታችንን ለፍርድ ያቀረቡት አይሁድ ጲላጦስ እነርሱ ወደ ተሰባሰቡበት ቦታ ወጥቶ ‹‹ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደል ምንድን ነው?›› ሲል በጠየቃቸው ጊዜ በቂ ምላሽ አላቀረቡም፡፡

በግብረ ሕማማት‹‹የማይሞት መለኮት ስለ እኛ የሞትን ጽዋ ተቀብሎ በሰውነቱ ሞተ! ወዮ ለዚህ አንክሮ ይገባል፡፡›› እንደተባለ ስለኛ በፈቃዱ ይሞት ዘንድ ፈቃዱ ነበርና በአይሁድ ጭካኔ ምክንያትነት ሞት ተፈረደበት፡፡ 

ቀዳም ስዑር

በሰሙነ ሕማማት በስቀለት ማግስት የሚውለው ቅዳሜ ቀዳም ሥዑር በመባል ይጠራል፡፡ በዚህ ዕለት ከድሮው በተለየ መልኩ ጌታችን መድኂታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምና ልጆቹን ከዲያብሎስ አገዛዝና እስራት ነጻ ለማውጣት የተቀበለውን መከራ፣ እንዲሁም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ማደሩን በማሰብ በጾም ታስቦ ስለሚውል ቀዳም ስዑር ወይም የተሻረው ቅዳሜ ተብሏል፡፡ የማይጾመው ቅዳሜ ስለሚጾም ስዑር /የተሻረ/ ተብሏል፡፡

የቀዳም ስዑር  ሌሎች ስያሜዎች ለምለም ቅዳሜና ቅዱስ ቅዳሜ ይባላሉ።

እነዚህን ሣምንታት በጾምና በፀሎት ያሳለፈው ሕዝበ ክርስቲያን ለታላቁ ትንሣኤ በዓል ይደርሳል።

ትንሣኤ ማለት ተንሥአ ካለው የግዕዝ ግሥ የተወረሰ ሲሆን፣ ትርጉሙም መነሣት ወይም አነሣሥ ማለት ነው።

እስራኤል ዘሥጋ ያከብሩት የነበረው በዓለ ፋሲካ ከባርነት ቀንበር ወደ ነጻነት የተላለፉበት ከኀዘን ወደ ደስታ የተሸጋገሩበት በዓል ነበር ።

የሐዲስ ኪዳን በዓለ ትንሣኤ ግን እሥራኤል ዘነፍስ ከኃጢዓት ወደ ጽድቅ የተመለስንበት ከአሳር ወደ ክብር፤   ከአሮጌው ወደ ሐዲስ ሕይወት መሸጋገሪያ መንፈሳዊ የነጻነት በዓል ነው ።
ከማኅበረ ቅዱሳን የተገኘው መረጃ ደግሞ "ትንሣኤ"የሚለው ቃል የግእዝ ቃል መገኛው "ተንሥአ = ተነሣ" የሚለው ግሥ ሲሆን፣ ትርጕሙም መነሣት፣ አነሣሥ፣ አዲስ ሕይወትን ማግኘት ማለት ነው፡፡ 

"ትንሣኤ" በየመልኩና በየዓይነቱ ሲተረጐም አምስት ክፍሎች አሉት፦
የመጀመሪያው ትንሣኤ ሕሊና ነው፤ ይህም ማለት ተዘክሮተ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን ማሰብ) ነው፡፡
ሁለተኛውም ትንሣኤ ልቡና ነው፤ የዚህም ምሥጢሩ ቃለ እግዘብሔርን መስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር ነው፡፡
ሦስተኛው ትንሣኤ ለጊዜው (በተአምራት) የሙታን በሥጋ መነሣት ነው፡፡ ነገር ግን በድጋሚ ሌላ ሞት ይከተለዋል፡፡
አራተኛው ትንሣኤ ክርስቶስ በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን ያመላክታል፡፡
አምስተኛው የትንሣኤ ደረጃ የባሕርይ አምላክ የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ መሠረት ያደረገ ትንሣኤ ዘጉባኤ ሲሆን፣ ይህም ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው እንደየሥራው ለክብርና ለውርደት፣ ለጽድቅና ለኵነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ  በማለት ያብራራል፡፡

የትንሣኤ ሌላኛው መጠሪያ ፋሲካ ነው።የቃሉ መነሻ የዓረብኛው ፓስኻ ነው።የፓስኻ ትርጉሙም ማዕዶት መሸጋገሪያ ማለት ነው ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀልን ፀዋትወ መከራ ተቀብሎ በመስቀል ላይ ሞቶ፥ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሙታንን በሞቱ ሕያዋን ያደርጋቸው ዘንድ ሞተ፡፡ በዕለተ ዓርብ የፈጠረውን አዳም በፈጸመው በደል ከተፈረደበት የሞት ፍርድ ነፃ ይሆንዘንድ፥ በባሕርዩ ሞት የሌለበት አምላክ በዕለተ ዓርብ መስቀል ላይ ዋለ፡፡ 
ወዳጆቹ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በመስቀል ላይ የዋለውን ሥጋውን አውርደው፥ለመቅበር፤ ከገዥው ከጲላጦስ ለምነው እንዲቀብሩ ተፈቀደላቸው፡፡  ከመስቀሉ አወረዱት እንደ ቤተ አይሁድ የአቀባበር ሥርዓትና ልማድ የደቀቀና መዓዛው   የጣፈጠ ሽቱ አዘጋጅተው፥ ከጥሩ ሐር በተሠራ በፍታአ ገንዘው ዮሴፍ ለራሱ አስወቅሮ ባሳነፀው አዲስ መቃብር ቀበሩት ይሉናል በእምነቱ ላይ የተዘጋጁ መዛግብት።

በሕይወተ ሥጋ ሳለ በሦስተኛው ቀን እነሳለሁ ብሏልና ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት ሰርቀው፥ ወስደው ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ብለው ሕዝቡን እንዳያስቱ መቃብሩ ይጠበቅ በማለት ወስነው በእያንዳንዱ አራት አባላት ያሉባቸው በሦስት ፈረቃዎች የሚጠብቅ የጭፍራ ቡድን ተመድቦ መቃብሩን በንቃትና በጥንቃቄ  ጠብቀዋል፡፡ ባለሥልጣናትም ጭፍራው ባለበት መቃብሩን አስቆልፈው በየቀለበታቸው (ማኅተማቸው) አትመውት ነበር፡፡ 

ሰውን ለማዳን በፈቃዱ ባደረገው የቸርነት ሥራ፥ በሥጋ ቢሞትም፤ በባሕርዩ ሞት የሌለበትን ጌታ ሞትና መቃብር ይዘው ሊያስቀሩት የማይቻላቸው በመሆኑ፤ ኃጢዓትን፣ሞትንና መቃብርን ደምስሶ፥ መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ፣ ሳይል በሦስተኛው ቀን በሌሊተ እሑድ ከሞት ተነሥቷል፡፡ 

በመቃብሩ ላይ ተገጥሞ የነበረው ድንጋይ ተገለባብጦ የተጠቀለለበት የከፈን ጨርቅ  መቃብሩ አፍ ላይ ተቀምጦ ተገኝቷል፡፡ለጥበቃ ተመርጠው ልዩ መመሪያና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው የነበሩ ጭፍሮችም ራሳቸውን እንኳ መጠበቅ ተስኗአቸው በያሉበት ወድቀው እንደ በድን ሆነው ነበር፡፡ 
ትንሣኤውን ለማየት ወደ መቃብሩ ሲመላለሱ ያነጉት ቅዱሳት አንስት ከሞት የተነሳውን ክርስቶስን ለማየት ቀዳሚ ዕድል ነበራቸው፡፡ አስቀድማ ለማየት የበቃችው ማርያም መግደላዊት መሆኗን ቅዱስ ወንጌል አስቀምጦታል፡፡ ከእሷ ተከትለው ሌሎችሞ ሴቶች አይተዋል፡፡

ክርሰቶስ በተነሳ ጊዜ፥ መልኩ እንደ ፀሐይ በሚያበራ ልብስ እንደ በረዶ በነጣ ግርማ ርእየቱ በሚያስፈራ ሁኔታ ተገልጦ ነበር፡፡ ሴቶቹንም “አይዞአችሁ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ ዐውቃለሁ፤ እሱ ከዚህ የለም እነሳለሁ እንዳለ ተነሥቷል፡፡ ነገር ግን ኑ የተቀበረበትን ቦታ እዩ ካያችሁም በኋላ ፈጥናችሁ  ሄዳችሁ  ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሯቸው በገሊላ ይቀድማችኋል በገሊላ ታዩታላችሁ” ብሏቸው ወደ መቃብሩ እየመራ ወሰዳቸው፡፡

ሴቶቹም ፍርሃትና ድንጋጤ በተቀላቀለበት የደስታ መንፈስ ተውጠው ወደ መቃብሩ ሄዱ፡፡ ፍርሃት የእግዚአብሔርን መልክ ማየታቸው፤ ደስታው ደግሞ፥ ትንሣኤውን መስማታቸው ነው፡፡ በደስታ ተሞልተው ዜናውን ለደቀ መዛሙርቱ ነግረው፥ እየተቻኮሉ ሲሄዱ ጌታችንን በመንገድ ተገለጠላቸው፡፡

“እንዴት ሰነበታችሁ! አስታረቅኋችሁ” አላቸው፡፡ቀርበውም ሰገዱለት፤ እሱም አይዞአችሁ አትፍሩ፤ ሂዱ ለወንድሞቻችሁ ገሊላ ይሂዱ ዘንድ ንገሩአቸው በዚያ ያዩኛል” አላቸው፡፡ ዐሥራ አንዱ ሐዋርያትም ዜናውን ሰምተው ወደተባሉበት ቦታ ወደ ገሊላ ሄዱ፡፡ በዚያም ጌታችንን ከሙታን ተነሥቶ አዩት፤ ሰገዱለትም ይላሉ መረጃዎቹ።

የክርስቶስ ትንሣኤ በስሙ ላመኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ትንሣኤ ነው፡፡ ክርስቶስ ለሙታን ሁሉ በኩር ሆኖ ተነሥቷል፡፡ የሙታንን ሁሉ መነሣት የሚያረጋግጥልን የጌታ ትንሣኤ ነው፡፡
የክርስቶስ ትንሣኤ መርገመ ሥጋ፥መርገመ ነፍስ፤ ሞተ ሥጋ፥ ሞተ ነፍስ የተሻረበት ርደተ ገሃነም ጠፍቶ፥ በአዳም የተፈረደው ፍርድ ሁሉተደምስሶ፤ ፍጹም ነፃነት፣ የማይለወጥ ደስታ፣ የተገኘበትጨበመሆኑ ፋሲካ ይባላል፡፡

ፋሲካ ደስታ ነው። እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነፃ የወጡበትን ቀን ነው።የእርቅ፣ የሰላም፣ የድኅነት ቀን ነው ከሞት ከመነሳት ከመቃብር ጨለማ ከመውጣት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ከመላቀቅ፥ ከሲኦል እስራት የተፈቱበት ጌታችን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መከራ ተቀብሎ የሞተው፥ ለመላው የሰው ዘር ለአዳም ልጆች ሁሉ ነው፡፡ ቤተሰብና ዘመድ ወዳጅና ጠላት ወንዝና አካባቢ ብሎ የሚለው ነገር አልነበረውም፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሰቀል ላይ የተቸነከረውና የሞተልን የወደደንና መከራ የተቀበለው እኛ ስለወደድነው ሳይሆን እሱ ስለወደደን ብቻ ነው፡፡
ዛሬም ያደረገልንንና ያደለንን አስበን፥ ፍቅሩን ተገንዝበን፣ለሰው በጎ ማድረግ፤ በፍቅሩ መመላለስ ያዳግተናል፡፡ ከሁሉም የሚረቀውና የሚደንቀው ያጠፋን የበደልን፣ በጥፋታችን ሞትን በራሳችን ላይ ያመጣን እኛ ሆነን፥ እሱ በደል ተላልፎ በእኛ የተፈረደውን የሞት ፍርድ ተቀብሎ መሞቱ ይደነቃል፡፡ 

ትንሣኤ በተከበረ በሳምንቱ ሌላ በዓል ይከበራል።በዓሉን በሁለንተናዊ መልኩ የሚደግም በዓል ነው።

ዳግም ትንሣኤ 
ከትንሣኤ በዓል በሣምንቱ ሌላ የትንሣኤ በዓል ይከበራል።ስሙም ዳግም ትንሣኤ ይባላል።
ዳግም ትንሣኤ የተባለበት  በአከባበርና በሥርዓቱ የመጀመሪያውን ትንሣኤ ስለሚመስል ነው፡፡የትንሣኤ ዕለት የሚባለው ቃለ እግዚአብሔር ሳይለወጥ፤በሙሉ በዚህ ቀን ይደገማል፡፡

ዳግም ትንሣኤ ሌሎች ሁለት መጠሪያዎችም አሉት፡፡አንደኛው “ፈጸምነ" እና አግብኣተ ግብር ” ይባላሉ፡፡ 
“ፈጸምነ” የተባለበት የሰሙነ ትንሣኤን በዓል አክብረን ፈጸምን ለማለት ነው፡፡ 
“አግብዖተ ግብር” የተባለበትም፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አባ ወአቡየ ግብር ዘወሀብከኒ ፈጸምኩ... እኔ ልሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርሁህ” ያለውን ከቅዳሴ በኋላ በሊቃውንት በዚህ ቀን ስለሚዘመር ነው፡፡

መልካም የትንሣኤ በዓል!!!

 





በዓላትየትንሣኤ በዓል

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!