እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:44:22 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ኢኮኖሚ

ነዳጅ ለቁልፍ ዘርፎች በቅድሚያ እንዲሰጥ ታዘዘ

2 ደቂቃ ንባብ
ነዳጅ ለቁልፍ ዘርፎች በቅድሚያ እንዲሰጥ ታዘዘ
የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎችና ማደያዎች ነዳጅ ለተወሰኑ ቁልፍ ዘርፎች ቅድሚያ እንዲሰጡ አዟል።

የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎችና ማደያዎች ነዳጅ ለተወሰኑ ቁልፍ ዘርፎች ቅድሚያ እንዲሰጡ አዘዙ። ወደ

አንዳንድ የእስያ አገሮች ነዳጅ የሚቆጥቡባቸውን እርምጃዎች መውሰድ ጀምረዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ዛሬ ለነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ባሰራጨው መመሪያ እንዳመለከተው፤በመካከለኛው ምሥራቅ በተከሰተው ቀውስ ሳቢያ ሊያጋጥም የሚችለውን የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ለመቋቋም መመሪያውን አውጥቷል፡፡

መመሪያው ለነዳጅ ግዥ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከግምት ውስጥ በማስገባትና አቅርቦቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት እንደተዘረጋ አመልክቷል።

በመመሪያው መሠረት  መጠናቀቅ ላይ ያሉና ለአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች፣ ለጸጥታና የደህንነት ሥራዎች የሚውሉ ተሽከርካሪዎችና መሠረታዊ ሸቀጦችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡

እንዲሁም ምርታቸውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ተቋማት  በአቅርቦት ቅድሚያ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ተወስኗል።

በተጨማሪም በነዳጅ ማደያዎች አካባቢ የሚታዩ የሥርጭት ግድፈቶችን ለመከላከል ጥብቅ ትዕዛዝ ባለሥልጣኑ አስተላልፏል።

ከነዚህም ማንኛውም የነዳጅ ማደያ ለሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ የመስጠት ግዴታ የተጣለበት ሲሆን፣ ከተሽከርካሪው የነዳጅ ታንከር ውጭ መቅዳት ተከልክሏል ብሏል መመሪያው፡፡

በዚህም ምክንያት በተጨማሪ መያዣ፣ ጋሎን፣ በርሜል ወይም ጀሪካን ነዳጅ መቅዳት በጥብቅ ተከልክሏል። 

ባለሥልጣኑ ክልከላውን ጥሰው በሚገኙ ማደያዎች ላይ የማያዳግም አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም  አስጠንቅቋል። 

ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ከተነሱበት መነሻ እስከ መድረሻ ማደያቸው ድረስ ያለውን ጉዞ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግበትም ታዟል።

የክልልና የከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮዎች ከባለሥልጣኑ ጋር በመቀናጀት ማደያዎች መመሪያውን ማክበራቸውን እንዲከታተሉም ጥሪ ቀርቦላቸዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት ነዳጅን በቁጠባና ለታለመለት ዓላማ ብቻ መጠቀም እንደሚገባ የሰጡትን አቅጣጫ ተከትሎ መመሪያው መውጣቱ ተገልጿል። 

በነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የሚስተዋሉ የሕገ-ወጥ ግብይትና የሀብት ብክነት ችግሮችን ለመቀነስና የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዳይዳከም ለማድረግ ታልሞ መዘጋጀቱንም የባለሥልጣኑ መግለጫ ያብራራል።

አሜሪካና እሥራኤል በኢራን ላይ በከፈቱት ጦርነት ጋር ተያይዞ በደረሰው የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎልና የነዳጅ መሠረተ ልማት ተቋማት መጎዳታቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡

ኢራንም የዓለም 20በመቶ ያህል የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ ዘግታለች፡፡

በተለይ በወሽመጡ በኩል ነዳጅ የሚያስገቡት የእስያ አገሮች የግል ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ የገደቡና የመንግሥት ሥራ ቀናትን የቀነሱም እገሮች መኖራቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ነዳጅየነዳጅ ስርጭት መመሪያ

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!