
አፍሪካን በቅጡ ያላወቃት "ዘ ኢኮኖሚስት"የተባለው መጽሔት በአንድ ወቅት"ጨለማዋ አህጉር"ብሎ ይጽፋል።አፍሪካውያን አዎን መልካችን ጠቆር ያለ ነው።ነገር ግን ውስጣችን የፈካና የበራ።
መጽሔቱ ግን ጥቁርን የተጠቀመው እንዲያው የመልካችን ቀለም ሊያመላክት አልነበረም።ሁለመናችሁ የጠቆረ ነው።ምንም ተሰፋ የላችሁም-ሀብት የላችሁ፣ዕውቀት የላችሁ፣ቴክኖሎጂ የላችሁ።እያለ የችግሮችን መዓት ዘርዝሮ።እንዲያው ፈጣሪ ለጉድ የፈጠራችሁ ብሎ።ተስፋ ቢስ መሆናችንን አረዳን።
ይኸው መጽሔት ያንን ካተመ ጥቂት ዓመታት በኋላ ጨለምተኝነቱን ከላዩ ላይ ገፎ "አፍሪካ የተስፋዋ አሀጉር"ብሎ ጻፈ።ያኔ በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያስመዘግቡ 10 አገሮች አምስቱ የአፍሪካ አገሮች መሆናቸው ሲገለጽ፤መጽሔቱም ከተኛበት ነቃና ይህቺ ናት አፍሪካ ማለት ጀመረ።
መጽሔቱ ዳፍንታምና በነጭ አምላኪነት የተመሠረተ ዘረኛ አመለካከት የታጠረ በመሆኑ እንጂ፤አፍሪካም ያኔም ጨለማ አልነበረችም።
በአህጉሪቱ የሚከሰቱ ችግሮችና መሪዎቿ ተስፋዋን አደበዘዘውት ሊሆን ይችላል።በውስጧ የታቀፈችው የተፈጥሮና የሰው ሀብት ተስፋ ቢስ የሚያሰኛትና የሚያጨልማት አልነበረም።ዛሬ ድረስ የዘለቀው የተፈጥሮ ሀብቷን ለመዝረፍ የሚደረገው ጥረት የችግሮቿ ሁሉ ምንጭ መሆኑ ሳይዘነጋ።
የአፍሪካ የሰው ኃይል አውሮፓና አሜሪካን በጉልበቱና በዕውቀቱ ሀብታምም አድረጓል።ዛሬም በተለያዩ መንገዶች እየገባ ለሁለንተናዊ ዕድገታቸው አስተዋጽዖ አያደረገ ነው።
አፍሪካውያንን ትውልደ አፍሪካውያነ የስደት ኑሮ በቃን ያሉበት ዘመን መጥቷል።በአህጉሪቱ ሰርቶ መለወጥ ይቻላል የሚል አስተሳሰብ ገዢ ሆኖ መጥቷል።
አፍሪካ የወጣቶች አህጉር ናት፤የአህጉሪቱ አንድ አካል የሆነችው ኢትዮጵያም በወጣቶች የተሞላች አገር፡፡
ከአህጉሪቱ ሕዝብ 60በመቶው ወጣቶች ናቸው፡፡እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 በሥራ ከሚሰማራው ኃይል 500ሚሊዮን ወጣቶች ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2100 ላይ በዓለም ከሚኖሩት ወጣቶች 50በመቶ የሚሆኑ አፍሪካውያን እንደሚሆኑም መረጃዎች ያሳያሉ።
የአህጉሪቱ ወጣቶች ከዘመኑ ዕድገትና ለውጥ ጋር የሚሄዱ ተግባራትን ለማከናወን ዕድልም ተስፋም አላቸው።በተለይም በኢኖቪዬሸንን ቴክኖሎጂ፣በኢኮኖሚና በከተሞች ልማት ሊሰሩባቸው የሚችሉ መሰኮች ናቸው።
ወጣቶቹ በነዚህ መሰኮች ተሰማርተው ለመሥራት በቅድሚያ የራሳቸው ተነሳሽነት ወሳኝ ሲሆን፣የፈጠራ ችሎታ ያላቸው መሆንም ይጠበቅባቸዋል።
የገንዘብ፣የዕውቀትና የቴክኖሎጂ መሰል ድጋፍ ካገኙ፤ሥራ ፈጥረው ራሳቸውንና አገራቸውን የሚቀይሩም ይሆናሉ።
ከኢትዮጵያ ሕዝብ 70 በመቶው ወጣቶች መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።ከነዚህም 30በመቶዎቹ ከ15ዓመት በላይ የሆኑና አምራች ከሚባለው ምድብ የሚመደቡ ናቸው።
የአገሪቱ ወጣቶች በተለያዩ መሰኮች ተሰማርተው ሕይወታቸውን ይመራሉ።በዚህም ወጣቶቹ የአገሪቱ እንቅስቃሴ ሞተር በሆኑት መስኮች የሚያደርጉት ተሳትፎ በአገሪቱ ልማትና ዕድገት እየተንፀባረቀ ነው።
ዛሬ በኢትዮጵያ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቆ የመንግሥት ሥራ ተቀጥሮ መሥራት እንደ ብቸኛ አማራጭ መጠበቅ ጊዜ ያለፈበት አስተሳሰብ እየሆነ በመምጣት ላይ ነው።
ወጣቶች አነስተኛና ዝቅተኛ ግምት ይሰጣቸው ከነበሩ የሥራ መሰኮች አንስቶ እስከ ግዙፍ ፕሮጀከቶች ያላቸው ተሳትፎ እያደገ መጥቷል።የነገዋ አገር ተረካቢ የሆኑ ወጣቶች አለን እያሉ ነው።እዚህ ላይ ሥራ አጥነት የለም፤ የሱስ ተገዢ ሆነው ራሳቸውን፣ቤተሰባቸውንና አገራቸውን የሚጎዱ ወጣቶች የሉም ማለት ግን አይደለም።
በተሰማሩባቸው መሰኮች ሥራ ፈጥረው ራሳቸውን ያሳወቁ፣ታዋቂነትን አግኝተው፣ምርትና አገልግሎታቸውን ያስተዋወቁና የሚሸጡ ወጣቶች ብቅ እያሉ ነው።እነዚህን ተከትለው ራሳቸውን ወደ ሥራ ፈጠራ የሚያስገቡ ወጣቶችም በመከሰት ላይ ናቸው።
በሥራ ራሳቸውን ከቀየሩ ወጣቶች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፈተናን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ስኬታማ የሆነው ወጣት አርሶ አደር አብነት ዴላሞ ይገኝበታል።
በክልሉ ከምባታ ዞን፣ አዲሎ ዙሪያ ወረዳ፣ የሃሚዶ ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ሞዴል አርሶ አደር ነው።
አብነት የሚኖርበት አካባቢ በጣም በረሃማና የውሃ እጥረት የነበረበትና ለግብርና ሥራ ያልተመቸ ነበር።
ወጣቱ አርሶ አደር ለዚህ ስኬት እንዲበቃ መንግሥት "በአካባቢያችን ያለውን ፀጋ በመለየት በአግባቡ መጠቀም" የሚለውን ሃሳብ ተግባራዊ ማድረጉ ለስኬቱ መነሻ እንደሆነ ይናገራል፡፡
አሁን በረሃማ የነበረው አካባቢ አረንጓዴ ለብሷል፡፡ ግቢው ባህላዊና ዘመናዊ ቤቶችን አካቶ በአገር በቀልና የውጭ ዛፎች ተከቧል።
በሰው ሰራሽ ፏፏቴ(ፋውንቴን) የተዋበ፣ በጌጠኛ መተላለፊያ መንገዶችና በውብ አበቦች ያሸበረቀና በአዕዋፍ ዜማ የታጀበው ግቢ መንፈስን በሃሴት ይሞላል ይላል የግብርና ሚኒስቴር መረጃ፡፡
ወጣት አብነት በግቢው ዘመናዊ የሆቴል አገልግሎት (ሎጅ) የሚሰጥ መስሎ የሚታይ ለዓይን ማራኪ የሆነ ልብን የሚያሞቅ፣ ምቹና ፅዱ የሆነ የምድር ገነት መፍጠር ችሏል።
በአንድ ወቅት በአካባቢው ያለውን የውሃ ችግር ለማቃለል የተቀናጀ የግብርና ልማት ሥራዎችን ለማከናወን የውሃ ገንዳ በማስቆፈር ከ5 ሺህ ሜትሪክ ኪዩቢክ በላይ ውሃ መያዝ ችሎ ነበር፡፡
አብነት ያሰራው የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ፈንድቶ ፈራረሰበት፤ የያዘውም ውሃ ጥቅም ላይ ሳይውል በአካባቢው ያለማውን ነገር ሁሉ አበላሽቶበት መና እንዳስቀረው ያስታውሳል።ነገር ግን ይሄ ፈተና ወድቆ እንዲቀር አላደረገውም፡፡
"በሚገጥሙን ፈተናዎች መሸነፍ ሳይሆን፤ ፈተናውን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ድል ማድረግ ይቻላል" የሚለውን የመሪውን ሐሳብ ወደ ተግባር በመቀየር የገጠመውን ፈተና ወደ ድል ቀይሯል።
ሞዴል አርሶ አደር አብነት በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ከሦስት በላይ የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳዎችን በመቆፈር የግብርና ሥራውን በትጋት ይሰራል፡፡
የግብርናውን ዘርፍ ሥራዎችን ለማዘመን የሚያስችሉ የምርምር ሥራዎችን ለሚያካሂዱ ተመራማሪዎች ማረፊያ የሚሆን ሰፊ ሳሎን፣ ዘመናዊ የምግብ ማብሰያ (ማዕድ ቤት) እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ የመኝታ ክፍል ገንብቷል።ግንባታዎቹ ተመራማሪዎች የጥናትና ምርምር ሥራዎቻቸውን እንዲያከናውኑ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ገልጿል፡፡
በተጨማሪም ዘመናዊ የስብሰባ አዳራሽና ለተለያዩ እንግዶች ማረፊያ የሚሆን ዘመናዊ መኝታ ቤትን ገንብቷል አብነት።
አርሶ አደር አብነት በ10 ሄክታር መሬት በሚሆን ግቢውና የእርሻ ማሳው የተቀናጀ ግብርናን ዕውን በማድረግ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በሰብል ልማት፣ በቡናና በቅመማ ቅመም ልማት ተሰማርቷል።
እንዲሁም የገጠር ኮሪደር ልማትን እየተገበረ ሲሆን፣በዚህም ለ10 ወጣቶች በቋሚነትና ከ50 እስከ 80 ለሚደርሱ ወጣቶች በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ብርቱ ወጣት ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም በአካባቢው ለሚገኙ ከ400 በላይ አርሶ አደሮችን በመደገፍ ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ እያገዘ ይገኛል፡፡
በቀጣይ በአካባቢው የሚገኙ ባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ በክልሉና ብሎም በአገር ደረጃ ፋይዳ ያለው አገልግሎት የሚሰጥ ዘመናዊ የአርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግበት የተቀናጀ የግብርና ማዕከል ለመገንባት አቅዷል።
ለማዕከሉ ግንባታም ከአካባቢው 50 ሄክታር መሬት እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ ምላሹን እየተጠባበቀ መሆኑንም ተናግሯል።
በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ወጣት አርሶ አደር አብነት የራሱን አሻራ ለማኖር ትልቅ ርዕይ ሰንቆ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው። ከዚህም በውሃ አጠር አካባቢዎች ውሃን በማሰባሰብ የግብርና ልማት ሥራዎችን በጥናት ላይ የተደገፈ ሥራን ለማከናወን እየተንቀሳቀሰኩ እገኛለሁ ብሏል፡፡
እንደ ወጣት አብነት አይነት የአኗኗር ዘይቤን የሚከተሉ በርካታ አርሶ አደሮችን በየአካባቢው መፍጠር ከተቻለ ኢትዮጵያንም አፍሪካንንም መቀየር ይቻላል።
ይህቺ በመጣቶች እየተሞላችና ዛሬ ችግሮቿና መከራዎቿ ጎልተው የሚሰሙባት፤ሥራ ፈጣሪዎቿና ፈጠራዎቻቸው ብቅ እያሉባት አህጉርና አገር የዕድገትና ብልጽግናዋ ጊዜ ከአድማስ ወዲህ መሆኑ እየታየ ነው።አብነት-ለኢትዮጵያም፤ለአፍሪካም።
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!