እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
05:09:36 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ስፖርት

አገር አትሌቶቿን አነገሠች፤እነሱም...

2 ደቂቃ ንባብ
አገር አትሌቶቿን አነገሠች፤እነሱም...

ያሳለፍነው ሣምንት መጨረሻ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባዮች ያስጠሩ አትሌቶች የተከበሩበት ነበር።

ኢትዮጵያውያን  አትሌቶች ለአገራቸው በዋሉላት ልከ ነው ማለት ባይቻልም፤አገር  ውለታችሁን አትረሳም የማለት  ያህል ነው።ለአትሌቶቻችን ያለንን ምስጋናና ክብር ከፍቅር ጋር የተገለጸበትም ሆኖ አልፏል።

በአዲስ አበባ ከተማ በተገነባው "አዲስ ስፖርት ማዕከል" በኦሊሞፒክ ውጤታማ የሆኑ ታላላቅና ታዋቂ አትሌቶች ሐውልት ቆሞላቸዋል።አገርን አስከብረው፤እነሱም ተከበሩ።

በፓርኩም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ በአንጸባራቂ ድሎቻቸው ያውለበለቡ አትሌቶች ሐውልት ቆሟል።

ከወንዶቹ  ሻምበል አበበ ቢቂላ፣ማሞ ወልዴና ምሩፅ ይፍጠር እስከ ታምራት ቶላ ተካተዋል።

ከሴቶቹ ከአትሌቶች ፋጡማ ሮባ፣ደራርቱ ቱሉ እስከ አልማዝ አያናም ሐውልት ተሰርቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ"በአዲስ ስፖርት ፓርክ በኦሎምፒክ መድረክ ለሀገራችን የወርቅ ሜዳሊያ ላስገኙ የ15 አትሌቶቻችን የክብር ሐውልቶች  ደግሞ አንደኛው ማሳያ ተደርጎ ይቆጠራል"ብሏል ።

የትናንት ጀግኖችን በመዘከር ቀጣዩን የአገር ተረካቢ ትውልድ በአገር ፍቅር ስሜት ለመገንባት ሚና እንዳለውም አመላክቷል።

"በኦሎምፒክ መድረክ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ከፍ ላደረጉ አትሌቶችን የሚዘክሩ የክብር ሐውልቶች መቆማቸው፤ የጀግኖቻችንን ታሪክ ሕያው ከማድረግ ባለፈ፤ ለቀጣዩ ትውልድ ስፖርተኞች ታላቅ ተምሳሌት ይሆናሉ።"

ኢትዮጵያ ለአትሌቶቿ የሰጠችው ክብር በአትሌቲክስ ዓለም በሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙኃን ዘንድም በአድናቆት ተዘግቧል።በዓለም ደረጃ የምትወዳደረን የጎረቤታችን ኬንያ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችም ከማዕከሉ ምረቃ በላይ ባላነሰ ትኩረታቸው ለአትሌቶቹ የተሰጠው ክብር ላይ ነበር ማለት ይቻላል።

በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን አስተያየታቸውን የሰጡት አትሌቶች አስተያየት በሕይወት እያሉ ሐውልት ቆሞላቸው መዘከርን ያልጠበቁት ክስተት እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

አገር አትሌቶቿን አስታወሰች፤አከበረች።በሕይወት ያሉት ለተሰጣቸው ክብር ምስጋናቸውን አቅርበው።ትውልድ አርአያነታችንን ተከትሎ አገሩን ያስጠራ አሉ።

አትሌቶቹ ከተሰጣቸው ክብር በላይ የሆነውን ጉዳይም በሰጧቸው አስተያየቶችም ገልጸዋል።ከነዚህም አትሌት ቀነኒሳ በቀለ መንግሥት ለአንጋፋ አትሌቶች የሰጠው እውቅና ተተኪ አትሌቶችን የሚያበረታታ ነው ብሏል።

በኦሎምፒክ ውድድሮች የአገራቸውን ክብር ከፍ ላደረጉ ጀግና አትሌቶች የመታሰቢያ ሐውልት በመቆሙም  ኩራት እንደተሰማው በመግለጽ፤ ለዚህም ምስጋናውን አቅርቧል።

ኮማንደር ጥሩነሽ ዲባባ ሐውልቱ ከአገር ክብርና ከትውልድ ቅብብሎሽ ጋር የተሳሰረ  ግንኙነት ያለው መሆኑን አመልክታለች።

በነባር አትሌቶች ተነሳስታ ውጤታማ መሆኗን  ገልጻ፣ዛሬ ደግሞ ተተኪዎች የእኛን ሐውልት ሲያዩ  መነሳሳት ይፈጥርላቸዋል በማለት ተናግራለች።

ጀግኖችን በሕይወት እያሉ ማክበር ለሚመጣው ትውልድ ለአገሩ ትልቅ ሥራ እንዲሠራ መነሳሳት የሚፈጥርና ምሳሌ እንደሚሆንም ገልጻለች።

በፓርኩ ውስጥ የቆመው ሐውልት ትርጉም በቃላት የማይገለጽ መሆኑን የተናገረችው  ኮማንደር ፋጡማ ሮባ ናት።

"ሐውልታችን መቆሙ ለእኛም ሞራል ለሚቀጥለው ትውልድም ትምህርት ነው" የምትለው ፋጡማ፣ሐውልቱን ለትውልዶች የሚተርፍ የስኬት ማስታወሻ ነው  ብላዋለች።

"በሕይወት እያለሁ ታሪኬን የሚዘክር ሐውልት በመቆሙ ዳግም እንደተወለድኩ ሆኖ ተሰምቶኛል" ያለው ኮማንደር አትሌት ታምራት ቶላ፤ ለመንግሥት ምስጋናውን አቅርቧል።

ወጣቱ በስፋት የተገነቡ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የመሮጫ ትራኮችን ተጠቅሞ የአገሩን ስም እንዲያስጠራ መልዕክቱን አስተላልፏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፓርኩ  ለጀግኖች አትሌቶች የክብር መግለጫ፣ ለወጣቶች የተስፋ ምንጭ፣ ለልጆች ደግሞ የደስታ ስጦታ ሆኖ መሰራቱን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአገር ግንባታና የሰው ልማትን በማህበራዊ መስተጋብር ጭምር እንደሚገነባ አስረድተዋል።

በፓርኩ ሐውልት የቆመላቸው ምርጥ  አትሌቶች ሐውልቶች ለትውልድ ምሳሌ የሆኑና ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያስጠሩ መሆናቸውን መስክረዋል።

አገር አትሌቶቿን በአደባባይ አነገሠች፤እነሱም በዓለም የሩጫ አደባባዮች የነገሡበትን ድል፤በአገራቸው መዲና ንግሥናቸውን በደስታና በክብር ተቀበሉ።

















  














 

ስፖርትአትሌቲክስ

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!