እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:45:38 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ኢኮኖሚ

አፍሪኤግዚም ባንክ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር አተረፈ

2 ደቂቃ ንባብ
አፍሪኤግዚም ባንክ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር አተረፈ
ባንኩ ከቀዳሚው ዓመት በ973ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የበለጠና የ19 በመቶ ብልጫ የተመዘገበበት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማስመዝገቡን አስታውቋል።

የአፍሪካ ኤክስፖርት ኢምፖርት(አፍሪኤግዚም)ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 1 ነጥብ 2ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቱን ዛሬ አስታወቀ።

ባንኩ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር  2025 የነበረው ጠቅላላ ሀብት 48 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ገልጿል።

የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ከቀዳሚው ዓመት 21 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።

በአንድ ዓመት ልዩነት የጠቅላላ ሀብቱ መጠን ከ40 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ወደ 48 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ተመንድጓል።

ባንኩ "ዕድገቱ የባንኩን ተከታታይነት ያለው አቅጣጫ አመላካች ነው" ብሎታል።

በበጀት ዓመቱ 33 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ብድር የሰጠ ሲሆን፣ይህም ከቀዳሚው የ16 በመቶ ብልጫ እንደተመዘገበበት አስረድቷል።በቀዳሚው ዓመት የተሰጠው ብድር 29 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር በማስታወስ።

ብድሩ በአፍሪካና በካሪቢያን አገሮች ለሚገኙ ተቋማት ሥራ ማስፋፊያና ማጠናከሪያ መሰጠቱንና ብድሩ ከተሰጣቸው መስኮች መካከል የማምረቻ(ማኑፋክቸሪንግ)፣የመሠረተ ልማት፣የምግብ ዋስትናና የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ዘርፎች ይገኙበታል ብሏል ባንኩ።

የባንኩ የተበላሸ ብድር ከአጠቃላይ ብድር ከሁለት ነጥብ አራት በመቶ ወደ ሁለት ነጥብ ሦስት በመቶ መቀነሱንና ይህም በዘርፉ የሚጠበቅ መሆኑን አመልክቶ፣በዚህም ባንኩ አስተማማኝና ጥራቱን እንዳስጠበቀ መሆኑንም ገልጿል።

የባንኩ ገቢ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በስድስት በመቶ አድጎ 3ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣የቀዳሚው ዓመት አፈጻጸም 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር አስታውቋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በጃፓንና በቻይና 800ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ቦንዶች በመግዛት የአክሲዮን ድርሻውን ማጠናከሩን የገለጸው የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት፣በሁለቱ አገሮች የተገዙት ቦንዶች የባንኩን አፍሪካዊ መሠረትና ማንነት በጠበቀ መልኩ ዘላቂና አስተማማኝ አቋሙን ያጠናከረ ሁለገብ የፋይናንስ ተቋም ሆኖ ከመሥራት አይገድበኝም ብሏል።

ባንኩ ከቀዳሚው ዓመት በ973 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የበለጠና የ19 በመቶ ብልጫ የተመዘገበበት ትርፍ ማግኘቱን ገልጿል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማስመዝገቡን አስታውቋል።

ትርፉ ፋይናንስ ነክ ከሆኑና ከምክር አገልግሎት መገኘቱንና ከነዚህም ንግድ፣ኢንዱስትሪና በኢኮኖሚ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የሚደግፉ ተግባራት እንደሚገኙበት አስረድቷል።

የባንኩ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት ዴኒስ ዴኒያ ባንኩ ዓለም በጂዖፖለቲካል ቀውስና ፈተናዎች በገጠማትና አንዳንድ ደረጃ ሰጪ ተቋማት በባንኩ ደረጃ መውረዱን በገለጹበት ዓመት ጥሩ አፈጻጸም ማስመዘገቡን አስታውቀዋል።

አፈጻጸሙ ባንኩ በስድስተኛው ስትራቴጂያዊ ዕቅዱ በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት ለማሳካት የያዘውን ዕቅድ አስቀድሞ እያሳካ መሄዱን ያሳያል ብለዋል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የአፍሪካ ኤክስፖርት ኢምፖርት(አፍሪኤግዚም)ባንክ ከ30ዓመታት በፊት የተመሠረተ በአፍሪካና ካሪቢያን አገሮች የሚንቀሳቀስና ትርፋማ የሆነ ባንክ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።






 

ኢኮኖሚባንክና ፋይናንስ

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!