እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
05:10:16 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ማህበራዊ

አፍሪካ በአንጋፋዋ ዲፕሎማት ሞት ኀዘን ላይ ናት

2 ደቂቃ ንባብ
አፍሪካ በአንጋፋዋ ዲፕሎማት ሞት ኀዘን ላይ ናት
አምባሳደር ቆንጂት ለኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካን ጥቅም ለማስከበርና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር የነበራቸው የማይናወጥ ቁርጠኝነት ለአህጉራዊ የጋራ ግቦች መሳካት የጎላ ሚና ነበረው።
አፍሪካ በአንጋፋ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ ሞት ኀዘን ላይ ናት።

አንጋፋዋ ዲፕሎማት "የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ኢንሳይክሎፒዲያ" ተብለው ይታወቁ ነበር።


ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት(አአድ)ወቅት ካገለገሉ ቀደምት ዲፕሎማቶች መካከል የሚጠቀሱ፤ድርጅቱ ወደ አፍሪካ ኅብረት ሲሸጋገርም ሙያዊ አስተዋጽ አበርክተዋል።


አምባሳደር ቆንጂት በ19555 ሥራ ሲጀምሩ በኢትዮጽያ የዲፕሎማሲው መስክ ለሴቶች እምብዛም ክፍት አልነበረም።


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዕረፍታቸውን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ይህንንና ለአገራቸው ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አመላካች ነው።


"አምባሳደር ቆንጂት ከልጅነት እስከ ዕውቀት ኢትዮጵያን በዲፕሎማትነት በማገልገል፣ ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥለው ሁለተኛዋ ሴት የኢትዮጵያ አምባሳደር ናቸው። ለሕግ፣ ለአሠራር፣ ለፕሮቶኮል እና ለኢትዮጵያ ጥቅሞች በነበራቸው የጸና አቋም እናስታውሳቸዋለን። ከእርሳቸው በኋላ አያሌ ሴት ዲፕሎማቶች በመስኩ እንዲሠማሩ መንገዱን አስፍተዋል"ብለዋል።


የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ ዓሊ ዩሱፍ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ስመጥር በሆኑት አምባሳደር ቆንጂት ኅልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን ገልጸዋል።

ሊቀመንበሩ አምባሳደሯን የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ፈር ቀዳጅ፣ ታላቅ ዲፕሎማትና ሕይወታቸውን ለአገራቸውና ለአህጉሪቱ እድገት የሰጡ ጽኑ አፍሪካዊት ሲሉ አወድሰዋቸዋል።

አምባሳደር ቆንጂት ለአሥርት የዘለቀ አርአያነት ያለው ሙያዊ ስኬት ማስመዝገባቸውንና ከኢትዮጵያ ቀዳሚ ሴት አምባሳደሮች አንዷ በመሆንም ለአፍሪካውያን ሴት ዲፕሎማቶች የብርሃን ፋና መሆናቸውን አመልክተዋል።

የአፍሪካን ጥቅም ለማስከበርና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር የነበራቸው የማይናወጥ ቁርጠኝነት ለአህጉራዊ የጋራ ግቦች መሳካት የጎላ ሚና እንደነበረውም አውስተዋል።

ሊቀመንበሩ አምባሳደር ቆንጂት በታማኝነት፣ በልዩ ብቃትና ለጋራ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የነበራቸው ጽኑ ቁርጠኝነት የአፍሪካ ዲፕሎማሲ እሴቶች ያላቸውን ጽኑ አቋም ያሳየ ነው ብለዋል።

የአምባሳደር ቆንጂት የዲፕሎማሲ ዐሻራ ለቀጣይ ትውልድ ዲፕሎማቶች፣በተለይም ለሴቶች፣በድፍረትና በዓላማ እንዲያገለግሉ ዘላቂ መነሳሳት ሆኖ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።


ከግማሽ ክፍለ ዘመን ያለፈ አገልግሎት ያላቸው ዲፕሎማት በኒው ዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተመድበው በፀረ ቅኝ አገዛዝ ጉዳዮች የሚከታተል ክፍል ውስጥ ሲያገለግሉ ለአፍሪካ ነፃነት ግንባር ቀደም ሆነው መታየት የጀመሩባቸውን ተግባራት በማከናወን ዕውቅና ማግኘት የጀመሩበት ወቅት ነበር።


ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካውያን መብቶችና ጥቅሞች መከበር የታገሉት አምባሳደር ቆንጂት በ86ዓመታቸው ከዚህ ዓለም የተለዩት ዛሬ ነው።


አገራቸውን በኦስትሪያ፣በግብፅ፣በአሥራኤል፣በካናዳና በሜክሲኮ በአምባሳደርነት ማገልገላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።"ሥራዬ ሕይወቴ ነው፤ለእሱም ሕይወቴን ሰጥቼያለሁ"በሚል መርህም ሕይወታቸውን እንደሚመሩም በአንድ ወቅት ተናግረዋል።ይህንንም የሙያ ባልደረቦቻቸው ይመሰክሩላቸዋል።


ኢትዮጵያን በተከታታይ መንግሥታት በማገልገል ክብርና ምስጋና የተቸራቸው አንጋፋ ዲፕሎማት ሆነውም አገልግለዋል።


አምባሳደር ቆንጂት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዕወቅና የሰጡበትን ሽልማት ተቀብለዋል።


እንዲሁም በ2008የአዲስ  አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷቸዋል።


አምባሳደር  ቅንጂት ከጃፓን መንግሥትና ከታላላቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሽልማቶች መቀበላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።








ታዋቂ ሰዎችአምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!