እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
03:40:30 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ባህልና ኪነ-ጥበባት

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የአፍሪካ ባህል ስፖርቶችና ጨዋታዎች ፌስቲቫል ታዘጋጃለች

1 ደቂቃ ንባብ
ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የአፍሪካ ባህል ስፖርቶችና ጨዋታዎች ፌስቲቫል ታዘጋጃለች
በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት የመጀመሪያውን የአፍሪካ ባህል ስፖርቶችና ጨዋታዎች መልቲ-ኤቨንት ፌስቲቫል በኢትዮጵያ ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን የአፍሪካ የባህል ስፖርቶችና ጨዋታዎች ፌስቲቫል እንድታዘጋጅ ተመርጣለች።

የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ከአፍሪካ ባህል ስፖርቶችና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን ጋር በጋራ ለመስራት ዛሬ  ስምምነት ተፈራርሟል።

በስምምነቱ መሠረት በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት የመጀመሪያውን የአፍሪካ ባህል ስፖርቶችና ጨዋታዎች መልቲ-ኤቨንት ፌስቲቫል በኢትዮጵያ ይካሄዳል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ እንደተናገሩት፥ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ያላትን ጥንታዊና ደማቅ የባህል ስፖርት እሴቶች ከአህጉራዊው እንቅስቃሴ ጋር ለማስተሳሰር ያሰችላል፡፡

ፌስቲቫሉ በኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታ ሚና እንደሚኖረውም መግለጻቸውን የፋና ዘገባ ያመለክታል።

መንግሥት አገር በቀል ስፖርቶች እንዲያድጉና ለትውልድ እንዲተላለፉ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሕይወት መሐመድ በበኩላቸው፥ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች አዲስ ምዕራፍ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ኮንፌዴሬሽኑ በይፋ መቀላቀሏ ለአህጉራዊው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ይፈጥራል ያሉት ደግሞ የአፍሪካ ባህል ስፖርቶችና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን ሊቀመንበር ኪይካማቱዋ (ዶ/ር) ናቸው።

ፌስቲቫሉ የአፍሪካን ባህላዊ እሴቶች በስፖርት አማካይነት ለማስተሳሰር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝና የአፍሪካን ማንነት፣ አንድነትና ሰላም የምናከብርበት  መድረክ ነው ብለዋል።

ስምምነቱ ተቋማቱ በቴክኒክ ድጋፍ፣ በመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም፣ በባህላዊ ጨዋታዎች ሕጎች ዝግጅትና ስልጠና ዙሪያ በቅርበት ለመስራት እንደሚያስችላቸውም ተመላክቷል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ በኮንፌዴሬሽኑ ውስጥ ያላትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክርም በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡

ፌስቲቫሉ መላው አፍሪካውያን የየራሳቸውን ልዩ ባህላዊ ጨዋታዎች ይዘው የሚቀርቡበትና የአህጉሪቱ ወጣቶች የሚገናኙበትና የባህል ልውውጥ የሚያደርጉበት መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል ተብሏል።

 

ስፖርትየባህል ስፖርቶችባህል

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!