
ኢትዮጵያ ከዓለም አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ ጥረት እንደምታደርግ ይታወቃል።
ለዚህም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአንበሳውን ድርሻ የሚወሰድ ቢሆንም፤ሚነስቴር መሥሪያ ቤቶችና ሌሎች አግባብ ያላቸው አካላትም የየራሳቸውን ሚና የሚጫወቱበት ሁኔታ ዝግ አይደለም።
ዜጎችም የአገራቸው አምባሳደር ሆነው የድርሻቸውን የሚያበረክቱበት መንገድ መፍጠር ቢችሉ ተመራጭ ነው።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረች ሰነባብታለች፤አባል የምትሆንበትም ጊዜ ሩቅ እንደማይሆንም ይገመታል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)በያውንዴ፤ካሜሩን በዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) የሚኒስትሮች ጉባዔ በመካፈል ላይ ናቸው።
ከጉባዔው በተጎዳኝም ከሳዑዲ ዓረቢያ የዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ድርጅቶች ምክትል ገዥና የድርድር ቡድን መሪ ፋሪድ አል-አሳሊ ጋር ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱ በዋናነት ያተኮረው በሁለቱ አገሮች መካከል ባለው የገበያ ዕድል ድርድርና የንግድ ልውውጥን ማሳደግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ወደ ዓለም ንግድ ድርጅት ለመቀላቀል የምታደርገውን ድርድር በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት ለማጠናቀቅ ያላትን ጽኑ አቋምና ዝግጁነት በዝርዝር አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገው ጥረት ማጠናቀቂያው ላይ በደረሰበት በዚህ ወቅት፣ እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ ካሉ ጠንካራ የንግድ አጋሮች ጋር የሚደረጉ የሁለትዮሽ ድርድሮች ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገትና ለንግድ ሥርዓቱ መዘመን የላቀ ፋይዳ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
በመጪው ወር በጄኔቫ ከሚካሄደው የሥራ ቡድን ስብሰባ በፊት የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ስምምነቱን ለማጠናቀቅ ቀጣይ የቴክኒክ ድርድሮች በፍጥነት እንዲከወኑ በሁለቱ ወገኖች መካከል መግባባት ላይ ተደርሷል።
ሚኒስትሩ ያደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ኢትዮጵያ ወደ ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ለመቀላቀል የምታደርገውን ጉዞ የሚያፋጥንና የአገሪቱን የንግድ ጥቅሞች ይበልጥ የሚያረጋግጥ መሆኑንም መግለጫው አመላክቷል።
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!