
ኢትዮጵያና ቻይና በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ መሠረት የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት ለመፈራረም ከስምምነት ላይ ደረሱ።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከቻይና የፋይናንስ ሚኒስትር ላን ፎአን ጋር በቤጂንግ የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብር ዙሪያ አድርገዋል።
ውይይቱ በዋናነት ትኩረት ያደረገው የኢትዮጵያን የዕዳ ክፍያ ሽግሽግ በማጠናቀቅ፣ ነባር ፕሮጀክቶችን በማፋጠንና ለአዳዲስ ግዙፍ የልማት ሥራዎች ላይ የገንዘብ ድጋፍ በሚደረግባቸው መንገዶች ላይ ነበር።
አገሮቹ በዕዳ ሽግሽግ ረገድ የኢትዮጵያን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከርና ለኢኮኖሚ እድገት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መግለጫ አስታውቋል።
የቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍን ተከትሎ የሁለትዮሽ ስምምነቱን ለመፈረም ያላቸውን ዝግጁነት ያረጋገጡ ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያን የዕዳ ጫና ለመቀነስ እመርታ መሆኑንም ገልጸዋል።
በውይይቱ ቀደም ብለው የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁና የገንዘብ አጠቃቀሙ ቀልጣፋ እንዲሆን ወቅት አጽንዖት ተሰጥቶታል።
የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በቅርበት ለመከታተልና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታትም ተስማምተዋል።
በአዳዲስ ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክቶች ዙሪያ፣ በተለይም የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ለመገንባት በሚቻልበት የገንዘብ ድጋፍ ላይ ፍሬያማ ምክክርም ተደርጓል።
አውሮፕላን ማረፊያው በኢትዮጵያ፣ በቻይናና በዓለም አቀፍ ገበያ መካከል ያለውን የንግድና የትራንስፖርት ትስስር እንደሚያሳድግም ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሁለቱ አገሮች ማዕከላዊ ባንኮች መካከል ስላለው ትብብርና ስለተደረሱ ስምምነቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ አህመድ በበኩላቸው ስምምነቱ በሁለቱ አገሮች መካከል ላለው የግንኙነት አዲስ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል።
አገሮቹ በቀጣይ የዕዳ ስምምነቱን ለመፈረምና የአውሮፕላን ማረፊያውን ፕሮጀክት ለማስጀመር ተቀራርበው ለመሥራት ከመግባባት ላይ መድረሳቸውንም መግለጫው አመልክቷል።
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!