እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:46:21 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ኢኮኖሚ

ኢትዮጵያና ጣልያን የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት ተፈራረሙ

1 ደቂቃ ንባብ
ኢትዮጵያና ጣልያን የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት ተፈራረሙ
ሰምምነቱ የሁለቱን አገሮች ስትራቴጂካዊ አጋርነት እንደሚያጠናክር ታምኖበታል።
ኢትዮጵያና ጣልያን ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን የሚያጠናክር የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱ የቡድን 20 አገሮች የጋራ ማዕቀፍ  የኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ  ሂደት አካል መሆኑ ተገልጿል።

ስምምነቱን  የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴና የጣልያን የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ጂያንካርሎ ጂኦርጌቲ ተፈራርመዋል።

አቶ አህመድ ስምምነቱ በተደረገበት ሥነ ሥርዓት ላይ የጣልያን መንግሥት ላደረገው ተሳትፎና አመራር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አገሪቱ የመግባቢያ ስምምነት ላይ ለመድረስና የሁለትዮሽ ስምምነቱን በስኬት ለማጠናቀቅ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል  ማለታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መግለጫ ያመለክታል።

ሚስተር ጂኦርጌቲ በበኩላቸው ስምምነቱ ኢትዮጵያ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ቅድሚያ ከምትሰጣቸው ጉዳዮች ጋር የተጣጣመ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር አገር በሆነችበት የጣልያን “የማቴይ እቅድ ለአፍሪካ” ስኬት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

በአቶ አሕመድ የተመራ ኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የአገሮቹን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ጉብኝት በሮም በማድረግ ላይ ይገኛል።

የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2022 ይፋ ያደረጉት የማቴይ ዕቅድ አገሪቱ ከአፍሪካ ጋር ያላት የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ለማጠናከር የተዘጋጀ ነው።

አገሪቱ ያሰናዳችው የ5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዩሮ ዕቅድ በጣልያን የብሔራዊ ዘይትና ነዳጅ ኩባንያ መሥራቹ ኤነሪኮ ማቴይ የተሰየመ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

ኩባንያው ከአፍሪካ ጋር ከአጭር ጊዜ እርዳታ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ትብብርን በማስቀደም በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የአፍሪካን የኢኮኖሚ ዕድገት መደገፍ፣ የሥራ ዕድልን ማስፋትና አፍሪካን የአውሮፓ የኢነርጂ አቅራቢ አጋር ማድረግ በዕቅዱ የተካተቱ ዓላማዎች ናቸው።

ለአፍሪካውያን የኢኮኖሚ ችግሮች መፍትሄ በመስጠት ኢ-መደበኛ ፍልሰትን መከላከልና የጋራ ተጠቃሚነትና ትብብር መፍጠርን ሌሎቹ የዕቅዱ ዓላማዎች ሆነው ይሰራባቸዋል።


ፋይናንስኢኮኖሚየዕዳ ሸግሽግ

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!