
ውልደቱ መጋቢት 30 ቀን 1938 አገልግሎት መስጠት የተጀመረ ነው።
ልጁ የተወለደው እንደ ማንኛውም ተወላጅ የራሱን ሕይወት በራሱ እስኪመራ በወላጆቹ ሥር እንዲመራ ነበር።
ለአቅመ አዳም ሲደርስ ደግሞ ራሱን ችሎ፣በትምህርት ራሱን አብቅቶና ጎጆ ቀልሶ በአዲስ ጎዳና ሕይወትንና ትውልድን እንዲያስቀጥል ነው።
ከዚያ ባለፈ ደግሞ በዕውቀቱ፣በሥራው፣በምግባሩና በማንነቱ ከራሱ አልፎ ወላጆቹን፣ ቤተሰቦቹንና ወገኖቹንና አገሩን አኩሪ እንዲሆን ይጠበቅበታል።
ታዲያ የተወለደ ልጅ ሁሉ የተባረከና የተቀደሰ ሆኖ አይገኝም።ጥቂቶች ግን ይህንን ያሟላሉ።ከአገር ተሻግረው አህጉርን ከዚያም አልፈው ለሰው ልጆች መድህን ሆነው ይገኛሉ።
ይህንን ወደ ተቋም ሰናሻግረው በትንሽ ደረጃ አገልግሎት ለመሰጠት ተፈጥረው በአገልግሎታቸው ለሌሎች የተረፉ ተቋማት እናገኛለን።የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነዚህ መካከል ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ዛሬ በዕለተ ልደቱ 80 ዓመታት ያስቆጠረውን ተቋም የዕድገት፣ የትርፋማነትና የአገር ኩራት ምሳሌ ሆኖ መዝለቁን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ አሁን ከ150 በላይ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመያዝ በዓመት ከ20 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን ማጓጓዝ ከሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
አየር መንገዱ 145 የዓለም አቀፍ እንዲሁም 23 የአገር ውስጥ መዳረሻዎች እንዳሉት ገልጸው፣በዚህም ከአፍሪካ ቀደሚው አየር መንገድ ለመሆን በቅቷል ብለዋል።
ዘመናቱ ለአየር መንገዱ የታታሪነት፣ የጠንክሮ መስራትና የስኬት ማሳያ መሆናቸውን በማመላከት።
ከዚህ አልፎ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ለማፋጠን ሚና በመወጣት ላይ የሚገኝ ተቋም ነው ሲሉም በዚህ ስድስት ሣምንታት በሚቆየውና በተለያዩ መርሐ ግብሮች በሚከበረው መርሐ ግብር መክፈቻ ላይ አሰታውቀዋል ።
አየር መንገዱ ፈተናዎች በጽናት በማለፍ አፍሪካን ከዓለም ጋር የሚያገናኝ ቀዳሚ የአቪዬሽን ተቋም መሆኑን በተግባር ማረጋገጡን አስታውቀዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ።
ባለፉት ዓመታት ባስመዘገበው ተከታታይ ዕድገት በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ 145 መዳረሻዎች ያሉት ግዙፍ አየር መንገድ ለመሆን መብቃቱን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ ዘመኑ ያፈራቸውን እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖች በመጠቀም ለደንበኞቹ የላቀ አገልግሎት እያቀረበ መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣በተለይም በተቋም ግንባታ ረገድ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት የራሱን አውሮፕላኖች ጥገና ማከናወን የሚያስችል ሙሉ አቅም የፈጠረ ሲሆን፣ ይህም ለተቋሙ ዘላቂ ዕድገት መሠረት መጣሉን አመላክተዋል።
የራሱ አቪዬሽን አካዳሚ ያለው አየር መንገድ፥ የአፍሪካ ትልቁን የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በመገንባት በታሪኩ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ስኬት አስመዝግቧል ብለዋል።
አየር መንገዱ ራዕዩን መሸከም የሚችል ብቁ የሰው ኃይል ማፍራትና የሥራ ሥነ-ምግባር ያለው ታታሪ ሠራተኛ በመፍጠርም ውጤታማ መሆኑን አመልክተዋል።
የካርጎ የጭነት አገልግሎት አቅሙን ማሳደጉንም አቶ መሥፍን አስታውቀዋል።
አየር መንገዱ የገነባቸው የተቀናጁ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና የደንበኞችን እርካታ ታሳቢ ያደረጉ አሰራሮች በዓለም አቀፍ የገበያ ውድድር ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥልና አስተማማኝ ዕድገት ለማስመዝገብ እንዳስቻሉት አስረድተዋል ።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2040 መዳረሻዎቹን ወደ 243፣ አውሮፕላኖቹን ወደ 350፣ የሚያጓጉዘውን ጭነት አሁን ካለበት በዓመት 850 ሺህ ቶን ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን ለማድረስ አቅዷል።
እንዲሁም የመንገደኞችን ቁጥር በዓመት ወደ 60 ሚሊየን ለማሳደግና ዓመታዊ ገቢውንም 30 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ እንደሚሰራ አቶ መሥፍን አስታወቀዋል።
አየር መንገዱ ከአውስትራሊያ በስተቀር ወደ ሁሉም አህጉሮች የሚበር፣አትራፊና ዝነኛና የበርካታ ሽልማቶች ባለቤት የሆነ በአፍሪካ አህጉር በቀዳሚነት ደረጃ የተቀመጠ ተቋም ነው።
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!