እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:48:16 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ

ካልታወቁ ምንጮች የሚጫኑ መተግበሪያዎችን መቆጣጠሪያ አሠራር ይፋ አደረገ

1 ደቂቃ ንባብ
ካልታወቁ ምንጮች የሚጫኑ መተግበሪያዎችን መቆጣጠሪያ አሠራር ይፋ አደረገ
ኩበንያው የሚዘረጋው አሠራር ተጠቃሚዎች በአጭበርባሪዎች ተገፋፍተውና ተቻኩለው አደገኛ መተግበሪያዎችን በመጫን ለግል መረጃ ስርቆት እንዳይጋለጡ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጿል።

ጎግል ኩባንያ  ካልታወቁ ምንጮች የሚጫኑ መተግበሪያዎችን ለመቆጣጠር የ24 ሰዓት የቆይታ ጊዜን የሚያስገድድ አዲስ አሠራር ይፋ አደረገ።

አሠራሩ በአንድሮይድ ስልኮች ላይ ካልታወቁ ምንጮች የሚጫኑ መተግበሪያዎችን (Sideloading) ለመቆጣጠር የ24 ሰዓት የቆይታ ጊዜ አስገዳጅ እንደሚያደርገው ተመላክቷል፡፡

ይህ "Advanced Flow" የተሰኘው አሠራር ተጠቃሚዎች በአጭበርባሪዎች ተገፋፍተውና ተቻኩለው አደገኛ መተግበሪያዎችን በመጫን ለግል መረጃ ስርቆት እንዳይጋለጡ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም አስረድቷል።

ኩባንያው ጥብቅ ቁጥጥር ያስፈለገው "Perseus" የተሰኘ አዲስና አደገኛ ቫይረስ እንዲሁም ሌሎች 17 የሚሆኑ የማልዌር ዝርያዎች የሰዎችን የባንክ መረጃና የዲጂታል ማንነት ዘረፋ ላይ በመሰማራታቸው ነው ብሏል።

አሠራሩ የPlay Protect የደህንነት መጠበቂያን በማጠናከር የተጠቃሚዎችን ስልክ ከአደጋ ለመታደግ ታቅዶ መዘጋጀቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ያሰራጨው መረጃ ያመለክታል።

እንደ ኩባንያው ገለጻ አዲሱ መመሪያ ተፈጻሚ የሚሆነው ማንነታቸው በጎግል ያልተረጋገጠ አልሚዎች (Unverified Developers) ለሚያበለጽጓቸው መተግበሪያዎች ብቻ ነው።

ተጠቃሚዎች መተግበሪያዎቹን ለመጫን ዴቨሎፐር ሞድን ማብራት፣ ስልካቸውን በድጋሚ ማስጀመር (Restart)ና ለ24 ሰዓት በትዕግሥት መጠበቅ ይኖርባቸዋል ሲልም ማብራሪያ ሰጥቷል። 

በዚህም በአጥቂዎችና በተጠቃሚዎች መካከል የጊዜ ልዩነት በመፍጠር ጥቃቱን ለመቀነስ ይረዳል ሲልም የአሠራሩን ጠቀሜታ አብራርቷል።

የኩባንያው ውሳኔ ከተለያዩ የመተግበሪያ አልሚዎችና የዲጂታል መብት ተሟጋቾች ትችት ቀርቦበታል።

አሠራሩ የግል ነፃነትን የሚገድብ፣ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለክትትል አሳልፎ የሚሰጥና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ወደ ዘርፉ እንዳይገቡ እንቅፋት ይፈጥራል በማለት።

ኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂሳይንስና ቴክኖሎጂ

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!