
ኮኬይን በረቀቀ መንገድ ደብቃ ለማስተላለፍ የሞከረች ተጠርጣሪ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ሥር ዋለች።
ዑጋንዳዊቷ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ ውስጥ በረቀቀ መልኩ 500 ግራም የሚመዝን ኮኬይን የተባለ አደንዛዥ ዕጽ ደብቃ ለማስተላለፍ ስትሞክር በቁጥጥር ሥር ውላለች፡፡
ከማላዊ ዋና ከተማ ሊሎንጌ ተነስቶ ፊሊፒንስ ማኒላ መዳረሻው የሆነው አውሮፕላን በቦሌ ዓለም-አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ትራንዚት ሲያደርግ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ደኅንነት ባለሙያዎች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በዘመናዊ መሣሪያዎች ባከናወኑት ጥብቅ ፍተሻና ቁጥጥር ኮኬይኑ ከነተጠርጣሪዋ ተይዟል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አደገኛ ዕጽዋት ቁጥጥርና ወንጀል ምርመራ ዘርፍ አባላትም ለተጨማሪ ምርመራ እንደተረከቡት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል ፡፡
በተጨማሪም በተከታታይ ቀናት ከለንደን በአዲስ አበባ በኩል ወደ ኬንያ በሚጓዝ አውሮፕላን 86 ኪሎ ግራም ደረቅ ጫት እንዲሁም ከኢጣሊያ ሚላን በቦሌ ዓለም-አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ወደ ኮንጎ ኪንሻሳ በሚበር አውሮፕላን 17 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም ጫት በሕገ-ወጥ መንገድ ለማዘዋወር ሙከራ ሲደረግ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ባለሙያዎች በቁጥጥር ሥር መዋሉም ተመላክቷል፡፡
በያዝነው ሣምንት መጀመሪያም ከአራት ኪሎ ግራም በላይ ኮኬይን በቦሌ ዓለም-አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ያስታወሰው መረጃው፤ ኢትዮጵያ የበርካታ አፍሪካ አገሮች መተላለፊያ ከመሆኗም ባሻገር፤ በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠረውን የፀጥታ መደፍረስ ተከትሎ ተመራጭ የትራንዚት ማዕከልነቷ በመጠናከሩ ከሰላማዊ ተጓዦች ጋር ተቀላቅለው በሕገ-ወጥ ተግባራት የሚሰማሩ በመኖራቸው እንደ ወትሮው ሁሉ በከፍተኛ ዝግጁነት ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ያደረገውን ሪፎርም ተከትሎ የላቁ ቴክኖሎጂዎች መጠቀም መቻሉ፤ የሰው ኃይል አቅም መገንባቱ እንዲሁም ግልጽ አሠራር መዘርጋቱ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚተላለፉ አደንዛዥ ዕጾችና ሌሎችንም ሕገ-ወጥ ቁሶች በከፍተኛ ደረጃ መቆጣጠሩን መረጃው አመልክቷል።
በቀጣይም በተዘረጋው የአሠራር ሥርዓት መሠረት የሚወሰዱ ተመሳሳይ የቁጥጥር እርምጃዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብሏል፡፡
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!