እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
03:42:21 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ሕግና ፍትሕ

ዓለም አቀፍ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪው ከነግብረ-አበሮቹ ተያዘ

3 ደቂቃ ንባብ
ዓለም አቀፍ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪው ከነግብረ-አበሮቹ ተያዘ
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ያደገ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተጠናከረ ምርመራና ክትትል በማድረግ ከ70 በላይ በሀገር ውስጥና በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎችን ከለየ በኋላ ዋናውን ተጠርጣሪ ጨምሮ 10 ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ተከታትሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራውን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

‎ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ በማዘዋወር፣ ከ100 በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገ ና ከ50 በላይ ሴቶች እንዲደፈሩ ያደረገው ይትባረክ ዳዊት (ክብሮም)ን ከዘጠኝ ግብረ-አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ አጠናቅቆ ለዐቃቤ ሕግ ተላከ፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እንደገለጸው ተቋሙ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከሚሰራ ድርጅት ጋር ባደረገው የመረጃ ልውውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፈለግ የነበረው አደገኛ ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ይትባረክ ዳዊት ዓለሙን በትግራይ ክልል ሽሬ ከተማ ላይ ፖሊስ በቅንጅት በቁጥጥር ሥር አውሏል።

ተጠርጣሪው በፓስፖርት ስሙ ይትባረክ ዳዊት ዓለሙ፣ ቤተሰቦቹ በልጅነቱ ያወጡለት ስም ጳውሎስ ዳዊት ወልዳይ፤ ወንጀል መስራት ሲጀምር የሚታወቅባቸው ስሞች አድሀኖም፣ ሱዳን ሀገር የሚታወቅበት ስም አህመድ፤ ሶማሊያ፣ ጅቡቲና ኬንያ የሚጠቀምበት ስም ሙኒር ሲሆን ክብሮም ደግሞ በስዊድን እና በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የሚጠቀምባቸው ሀሰተኛ ስሞች መሆናቸውን ፖሊስ በምርመራው አረጋግጧል፡፡

ፖሊስ እነዚህን ስሞች ለምርመራው አጋዥ አድርጎ ያደገ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተጠናከረ ምርመራና ክትትል በማድረግ ከ70 በላይ በሀገር ውስጥና በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ዋና ዋና የሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎችን ከለየ በኋላ ዋናውን ተጠርጣሪ ጨምሮ በአጠቃላይ 10 ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ተከታትሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራውን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ፖሊስ የተያዙትንም ሆነ ያልተያዙትን ተጠርጣሪዎች በወንጀሉ ያፈሩትን ሀብት በጥናት በመለየት ሌሎች ሀብቶቻቸውንና በባንክ የሚገኝ ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ በፍርድ ቤት እንዲታገድ ማድረጉን ገልጿል፡፡

ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪ ቡድኑ ከ2010  ጀምሮ በርካታ ወጣቶችን ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳን፣ ከኤርትራ፣ ከጅቡቲ፣ ከኬንያና ከሶማሊያ በመመልመል ወደ ሊቢያ በመውሰድ ሊቢያ ውስጥ ባዘጋጁት መጋዝን እንዲታገቱ በማድረግ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ ከቤተሰቦቻቸው በማስላክ፤ ገንዘብ ያልከፈሉትን በቀን አንድ ጊዜ ብቻ በትንሹ ምግብ እንዲመገቡ በማድረግ፣ በጎማ፣ በዱላና በኤሌክትሪክ ገመድ በሰንሰለት እጅ እና እግራቸውን አስረው በመግረፍና በማስገረፍ፣ የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ አቃጥለው ሰውነታቸው ላይ በማንጠባጠብ ከፍተኛ ስቃይ በማድረስ፣ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በመፈፀም በርካታ ሰዎች ሕይወታቸው እንዲያልፍ፣ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው፣ ሴቶች እንዲደፈሩና ከፍተኛ አካላዊና ሥነ-ልቡናዊ ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረጋቸውን ፖሊስ በምርመራ ማረጋገጥ ችሏል፡፡

ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ሊቢያ ውስጥ ተጎጂዎችን አግተው የሚያሰቃዩባቸው አምስት ማከማቻ መጋዘን እንዳላቸውና በዚህ አደገኛ ወንጀል ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ በህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ሲንቀሳቀስ እንደነበረ ፖሊስ በሰበሰበው ማስረጃ ማረጋገጡን አስታውቋል።

ከ100 በላይ ተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸውን በሀገር ወስጥና በውጭ ሀገር የምስክርነት ቃል መቀበሉንም ለኢዜአ በላከው መግለጫ ያመለክታል፡፡

ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሊቢያ፣ ሱዳን፣ ቤልጂዬም፣ እንግሊዝ፣ካናዳ፣ኖርዌይ፣ ኔዘርላንድ፣ሉግዘምበርግና ስዊዘርላንድ ከሚገኙ  16 ተጎጂዎች ቃል መቀበሉንም አሳውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሀገርና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለውን ይህንን ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ለመከላከል ዘመኑ ያፈራቸውን የምርመራ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በተሟላ ፖሊሳዊ ስብዕናና ሥነ-ምግባር እየተመራ በላቀ ቁርጠኝነት ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑንም አስረድቷል።

ተቋሙ ከሀገራት ጋር በፈጠረው የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነትም ዓለም አቀፍ የወንጀል ተፈላጊዎችን ጭምር በቁጥጥር ሥር አውሎ በተለያየ ጊዜ ምርመራ በማጣራት በሀገር ውስጥ በህግ እንዲጠየቁና የተወሰኑት ደግሞ ከሀገራት ጋር ባለው የወንጀለኛ ልውውጥ ስምምነት መሰረት ተላልፈው እንዲሰጡ እያደረገ ይገኛል፡፡

ይህን ውስብስብ ድንበር ተሸጋሪ የወንጀል ጉዳይ በተሳካ ሁኔታ እንዲጣራ ከፖሊስ ጋር በትብብር ለሰሩት ለፍትህ ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ለተባባሪወ ድርጅትና በጉዳዩ ላይ መረጃ ሲሰጡ ለነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ምስጋናውን አቅርቧል።

ኅብረተሰቡ ማንኛውንም የወንጀል ድርጊት ሲመለከት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp)፤ በ991 ነፃ የስልክ መስመር እና ሰው አልባ ፖሊስ ጣቢያ (SPS) በመጠቀም ወይም በአቅራቢያው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ቀርቦ ጥቆማ በመስጠት ትብብሩን እንዲያጠናክር ጠይቋል፡፡



ሕግና ፍትሕሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርወንጀልፖሊስ

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!