
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚካሂሄደው ንግድ ሕግና ሥርዓትን ጠብቆ እንዲካሄድ ቁጥጥርና ክትትልን እንደሚጠናከር ዛሬ በተካሄደ ባሳተፈ ስብሰባ አመላከተ፡፡
የከተማው አስተዳደር የሕግ ማስከበርና ቁጥጥር ንዑስ ኮሚቴ፤ ባለፉት ወራት የተከናወኑ የቁጥጥርና የሕግ ማስከበር ተግባራትን ከዐቢይ የጋራ ግብረ-ኃይል ጋር ገምግሟል፡፡
ንዑስ ኮሚቴው አፈጻጸሙን በዝርዝር በገመገመበት ወቅት ሕገ ወጥነትን በመግታትና የገበያ መረጋጋትን በማረጋገጥ ለከተማዋን ነዋሪዎች ምቹ የኑሮ ዘይቤ እንዲኖርና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡
በዚህም በኬላዎች ላይ የሚደረገውን ፍተሻ እንዲያጠናከር፣ የነዳጅ ማደያዎች አገልግሎት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግና 24 ሰዓት ክፍት እንዲሆኑ ማድረግ ፣ በኑሮ ውድነት ላይ ጫና የሚፈጥሩ ሕገ ወጥ ደላሎችና ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃዎች እንዲወሰድ ወስኗል፡፡
እንዲሁም ከመጪው የትንሣዔ የፋሲካ በዓል ጋር በተያያዘም የዋጋ ጭማሪና የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር የተጠናከረ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም የንግድ ሥርዓቱ ከደላላ ነፃ የሆነ የግብይት ሥርአት እንዲመራር በቁርጠኝነት እንዲሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል ይላል ከከተማው አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የተገኘው መረጃ፡፡
የከተማው አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊና የንዑስ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ መድረኩን በመሩበት ወቅት እንደገለጹት ላለፉት ሦስት ዓመታት ሕገ ወጥ ሥርዓትን በመቆጣጠር የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ንዑስ ኮሚቴዉ አመርቂ ዉጤቶችን ማሳየቱን ገልጸው፤ሕጋዊነትን ማስፈን ምርጫ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ አምስቱ ኬላዎች ላይ የሚደረገው የመጋዘን ፍተሻ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ስጋት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም፣ ነዳጅ በመደበቅና በማከማቸት ችግር የሚፈጥሩ አካላትን መታገስ አይገባንም ብለዋል።
በከተማዋ ያሉ የነዳጅ ማደያዎች 24 ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጡና ሕገ ወጥ ስርጭት እንዲቆም የጸጥታ መዋቅሩ በቁርጠኝነትና ከሌብነት በጸዳ መልኩ ሊንቀሳቀስ ይገባል ያሉት ኃላፊዋ፣ ከአሰራር የሚወጡ ነጋዴዎች ከስህተታቸው ታርመው ወደ ትክክለኛ የአሰራር ሂደት እንዲገቡ ማድረግ ይገባናል ሲሉም አሳስበዋል።
የከተማው አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሐቢባ ሲራጅ ምርት በሚደብቁና የሚያከማቹ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ምርተ ለነዋሪዎች ጋር በአግባቡ ማድረስ እንደሚገባ አመልክተው፣ ከዋጋ በላይ የሚሸጡና የንግድ ሥርዓቱን የሚያናጉ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባል በማለት አስገንዝበዋል።
የንግድ ሥርዓቱ በምሽትም ቀጣይነት እንዲኖረው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተግባራዊነቱ ላይ ወጥነት የማይታይበት በመሆኑ በአፋጣኝ ወደ ተግባር እንዲገባ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ቶፊቅ መደድ በበኩላቸው የከተማው አሰተዳደር የንግድ ማህበረሰብ ወዳልተገባ ሥርዓት እንዳይገቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መስራት እንደሚገባ ጠቁመው፣ የኢኮኖሚ አሻጥርን የሚያራምዱ ከገበያ ማዕከላት እስከ መደበኛ ግብይት ድረስ ያለውን ሰንሰለት መቆጣጠርና የዋጋ ጭማሪ በሚያድጉት ላይ ለሕግ ማቅረብ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የመንገድ ላይ ካሜራዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ በማስገባትና የትራፊክና የጸጥታ መዋቅሩ በቅንጅት በመስራት፣ ከተማዋ ያለምንም የጸጥታ ስጋት የንግድ እንቅስቃሴዋ እንዲቀጥል ብሎም ከነዳጅ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ጋር በአግባቡ መወጣት እንደሚገባም አሳስበዋል።
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!