እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:43:48 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ኢኮኖሚ

የአበበ ተተኪ ታወቁ

2 ደቂቃ ንባብ
የአበበ ተተኪ ታወቁ
በተለይም በአፍሪካ ላይ የሚዘግቡ ታላላቅ መገናኛ ብዙኃን የዓመቱን 100 ምርጥ ሰዎች ከመረጡ አበበ አዕምሮ ሥላሴ አንዱ እንደሚሆኑ አያጠራጥርም።

የዓለምን ኢኮኖሚ ከሚዘውሩ ሁለት ተቋማት አንደኛው የዓለም ገንዘብ ድርጅት(አይ ኤም ኤፍ)ነው።

ተቋሙን በአሁኑ ወቅት በመምራት ላይ የሚገኙት ክሪስታሊና ጆርጂባ ይባላሉ።የአፍሪካውን ክፍል የሚመሩት ደግሞ አበበ አዕምሮ ሥላሴ ናቸው።

አበበ በተቋሙ ላለፉት 22ዓመታት አገልግለዋል።አሁን በያዙት ኃላፊነት ለ10 ዓመታት ሰርተዋል።ተቋሙና አፍሪካ ሲታሰቡ ወሳኙ ሰው እሳቸው እንደሆኑ በኢኮኖሚከስና ቢዝነስ መስኮች የተሰማሩ ሰዎች ያውቃሉ።

ተቋሙ ከሰሃራ በስተ ደቡብ ለሚገኙ 45 አገሮች በሚሰጠው የፖሊሲ ምክር፣ብድርና የቴከኒክ ድጋፍ በስተጀርባ አበበ እንዳሉ እሙን ነው።

በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአፍሪካ ላይ የሚዘግቡ ታላላቅ መገናኛ ብዙኃን የዓመቱን 100 ምርጥ ሰዎች ከመረጡ አበበ አዕምሮ ሥላሴ አንዱ እንደሚሆኑ አያጠራጥርም።

አበበ ከቀጣዩ ወር(May 2026) ጀምሮ በጡረታ ይገለላሉ።

ከአሁኑ ኃላፊነታቸው አስቀድሞ የተቋሙ የአፍሪካ ክፍልን በምክትል ዳይሬክተርነት፣ለተቋሙ የፖርቱጋልና የደቡብ አፍሪካ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል።

በአፍሪካና በምሥራቅ አውሮፓ አገሮች በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ተቋሙን ወክለው ሰርተዋል።

አበበ ተቋሙን ከመቀላቀላቸው በፊት አገራቸው ኢትዮጽያን በሙያቸው አገልግለዋል።

በለንደን ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት ውስጥ መሥራታቸውንም መረጃዎች ያሳያሉ።ትምህርታቸውን በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስም የተከታተሉ ናቸው አበበ አዕምሮ ሥላሴ።

ታዲያ አበበ በማን ሊተኩ ነው?ከተባለ የተቋሙ ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ትናንት ፍንጭ ሰጥተዋል።

ተተኪው ዜይን ዜይዳን የሚባሉ ሞሪታኒያዊ ናቸው።

"ለተቋሙ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሚስተር ዜይን ዜይዳንን የአፍሪካ ክፍል ዳይሬክተር አድርጌ ለመሾም መፈለጌን አሳውቄያለሁ።ዜይን በተቋሙ ላይ ጥልቅ ዕውቀት፣ፍትሃዊነትና ጠንካራ የፖሊሲ ልምድ ያላቸው በመሆናቸው ከሰሃራ በስተ ደቡብ ያሉትን የአፍሪካ አገሮች ፍላጎት የሚያሟላ የፖሊሲ ምክር፣የፋይናንስና የአቅም ግንባታ ፍላጎት ያሟላሉ ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።

የተቋሙ የመካከለኛው ምሥራቅና የማዕከላዊ እስያ ክፍል ምክትል ዳይሬክተር ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት ታላሚው ተሿሚ፣ ከ20ዓመታት በላይ የተሻገረ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አውጪነትና የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ትብብር አላቸው።

በባህረ ሰላጤው አገሮች የሚያደርገውን ስትራቴጂያዊ ትብብር በማሳለጥን ቀጣናዊ ትብብርን በማስተባበርና በሪያድ የተቋሙ ማስተባበሪያ ቢሮ እንዲከፈት ሚና መጫወታቸውን ከተቋሙ የወጣው መግለጫ ይገልጻል።

ተቋሙ ከሰሃራ በስተደቡብ ባሉት የአፍሪካ አገሮች የሚያከናውቸውን ተግባራት በመደገፍ አዎንታዊ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውንም አመልክቷል።

ዜይዳን ተቋሙን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2012 ከመቀላቀላቸው በፊት አገራቸውን በጠቅላይ ሚኒስትርነት፣በማዕከላዊ ባንክ ገዢነትና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የኢኮኖሚ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።

ዜይዳን በአፕላይድ ማቲማቲክስ የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣የኒስ ዩኒቨርሲቲ በማክሮ ኢኮኖሚክስ የማስትሬት ዲግሪም መመረቃቸውን መግለጫው ያስረዳል።



ኢኮኖሚዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!