እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:45:42 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ስፖርት

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታዎች ይደረጋሉ

2 ደቂቃ ንባብ
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታዎች ይደረጋሉ
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በዓለማችን በየዓመቱ የሚካሄድ ታላቅ ውድድር ነው፡፡

የአውሮፓ ሻምፒንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ የመልስ ጨዋታዎች ዛሬ ምሸቱን ይደረጋሉ፡፡

የፖርቹጋሉ ክለብ ስፖርቲንግ ሊዝበን በሜዳው ቦዶ ግሊምትን ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ያስተናግዳል፡፡

ባለፈው ሣምንት በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ቦዶ ግሊምት 3 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜ የማለፍ ዕድሉን ያሰፋበትን ውጤት አስመዝግቧል ፡፡

ቦዶ ግሊምት በዚህ የውድድር ዓመት በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ብቅ  ካሉ ኮለቦች መካከል አንዱ ነው፡፡

የኖርዌዩ ክለብ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ማንቸስተር ሲቲ፣ ኢንተር ሚላንና አትሌቲኮ ማድሪድን የመሳሰሉ  ክለቦችን በማሸነፍ አድናቆትን አትርፏል፡፡

ሁለቱ ክለቦች በሚያስመዘግቡት ድምር ውጤት አሸናፊ በሩብ ፍጻሜው ውጤት ከአርሰናልና ባየር ሊቨርኩሰን አሸናፊ ጋር የሚያገናኛቸው ይሆናል፡፡

ከምሽቱ አምስት  ሰዓት ላይ ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ከሪያል ማድሪድ ጋር የመልስ ጨዋታውን ያካሂዳል፡፡

በሳንቲያጎ ቤርናባው በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ሪያል ማድሪድ 3 ለ 0 መርታቱ ይታወሳል፡፡

ሪያል ማድሪድ የመጀመሪያው ጨዋታ በጉዳት ምክንት ያመለጣቸው ክሊያን ምባፔ፣ አልቫሮ ካሬራስ፣ ዴቪድ አላባና ጁዲ ቤሊንግሃምን በስብስቡ እንደሚያካተት መረጃዎች ያመለክታሉ።

ክለቦቹ በሚያስመዘግቡት ድምር ውጤት መሠረት አሸናፊው በሩብ ፍጻሜው ከባየር ሙኒክና አታላንታ አሸናፊ ጋር ይገናኛል፡፡

ቼልሲ በተመሳሳይ ሰዓት ላይ የፈረንሳዩን ፒ ኤስ ጂ በስታምፎርድ ብሪጅ ያስተናግዳል፡፡በመጀመሪያው  ዙር ጨዋታ ፒ ኤስ ጂ 5 ለ 2 አሸንፎታል፡፡

ክለቦቹ ከ10 ዓመታት በፊት ተገናኝተው በሻምፒየንስ ሊግ  ፒ ኤስ ጂ በድምር ውጤት 4 ለ 2 በማሸነፍ ቼልሲን ከውድድሩ እንዳሰናበተው ዘገባዎች አስታውሰዋል፡፡

የክለቦቹ የድምር ውጤት አሸናፊ በሩብ ፍጻሜው ከሊቨርፑልና ጋላታሳራይ አሸናፊ ጋር እንደሚጋጠም የውደድሩ መርሐ ግብር ያመለክታል፡፡

አርሰናል በሜዳው ከባየር ሊቨርኩሰን ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ሌላኛው የምሸቱ ተጠባቂ ውድድር እንደሚሆን የብዙዎች ግምት ነው፡፡

ክለቦቹ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸውን አንድ አቻ ያጠናቀቁ ሲሆን፥ በድምር ውጤት አሸናፊ የሚሆነው ክለብ በሩብ ፍጻሜው ከቦዶ ግሊምትና ስፖርቲንግ ሊዝበን ክለቦች አሸናፊ ጋር ይገናኛል፡፡

ስፖርትእግር ኳስየአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!