እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
03:43:12 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ሕግና ፍትሕ

የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ ዓዋጅ ፀደቀ

2 ደቂቃ ንባብ
የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ ዓዋጅ ፀደቀ
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ ዓዋጅን በሁለት ተቃውሞ፤ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ ዓዋጅን ዛሬ አፀደቀ፡፡

የምክር ቤቱ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግሥቱ በምክር ቤቱ 13ኛ መደበኛ ስብሰባው ረቂቅ ዓዋጁ ከመጽደቁ በፊት ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

ረቂቅ ዓዋጁ በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት የወንጀል ፍርድ ሂደት የተጠርጣሪንና የተከሳሽን እንዲሁም በወንጀል ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች ለማክበርና ለማስከበር የሕግ የበላይነት በማስፈን የአሰራር ሥርዓትን ለመዘርጋት እንደሚያስችል ሰብሳቢዋ ገልጸዋል፡፡

የተቀላጠፈ የፍትህ ሥርዓት እንዲኖር ለማስቻልና ልዩ የወንጀል ምርመራ ዘዴን እንዲሁም ለተጎጂዎች ካሣ የሚከፈልበትን አግባብ ያካተተ ዓለም አቀፍ መርህን የተከተለ ረቂቅ ዓዋጅ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ረቂቅ ዓዋጁ ከኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥትና ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ መርሆዎችና እሴቶች እንዲሁም ከወንጀል ሕጉ ጋር የተጣጣመና ዘመናዊ መሆኑንም አብራረርተዋል፡፡

ረቂቅ ዓዋጁ በሕገ መንግሥቱ፣ በወንጀል ሕጉ፣ በዓለም አቀፍ ሕጎችና በሌሎች አግባብነት ባላቸው ሕጎች የተረጋገጡ ልዩ ትኩረት ለሚያሻቸው ለሴቶች፣ ህፃናትና አካል ጉዳተኞች የተሰጣቸውን መብቶች ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል ወይዘሮ እፀገነት።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ ረቂቅ ዓዋጁ የባለድርሻ ተሳትፎ በግልጽ የታየበትና ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ጭምር ማረጋገጫ እንደሰጡበት አስረድተዋል፡፡

ዜጎች ካለጥፋታቸው ማረሚያ ቤት ቆይተው ፍርድ ቤት ነፃ ሲላቸው ካሣ የሚከፈልበትን የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት ዓዋጁ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

የምክር  ቤቱ አፈ ጉባዔ  አቶ  ታገሰ ጫፎ  ዓዋጁ ዘመኑን የዋጀ ፣ ጊዜ ወስዶ የተሰራበት፣ለሌሎች ሕጎች ጭምር ትምህርት የሚወሰድበትና አስተማሪ የሆነ እንዲሁም የምክር ቤቱን አሰራር በግልጽ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በምክር ቤቱ የሚወጡ ሕጎች ከሕገ- መንግሥቱ የሚመነጩና የሕዝቡን የፍትህ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያግዙ መሆናቸውን መረዳት ይገባል ብለዋል ፡፡

ከፌዴራልና ከክልል መንግሥታት ግንኙነት ጋር በተያያዘ ረቂቅ ዓዋጅ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን አፈ ጉባኤው አስታውሰው፤ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ ዓዋጅም ከክልሎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተድርጎበት መዳበሩን ገልጸዋል።

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ረቂቅ ዓዋጁ ረጅም ጊዜ የቆየና የዘገየ ቢሆንም፤ በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታሲፈጥሩ የነበሩ ችግሮችን የሚፈታ ወቅቱን የሚመጥንና የፍትህ ሥርዓትን ለማስፈን እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊዊ መብቶችን ለማስከበርና የፍትህ ሥርዓቱን በማዘመን ወቅቱን የዋጁ አገልግሎት ለመስጠት ረቂቅ ዓዋጁ ሚናው የጎላ መሆኑን አባላቱ አመላክተዋል፡፡፡

ረቂቅ ዓዋጁ በአተገባበር ሂደት ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ታሳቢ በማድረግ ከፍትህ አካላት ጋር መወያየት እንደሚያስፈልግ የተናገሩ የምክር አባላትም ነበሩ፡፡

ከምርመራ ሂደትና ከዲጂታል አሰራሮች ጋር በተያያዘ የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብትን በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበት አስገንዝበው፤ በማረሚያ ቤት ቆይተው ፍርድ ቤት ነፃ የሚላቸው ዜጎች የካሳ ክፍያ ሥርዓትን ለመዘርጋት በግልጽ በረቂቅ ዓዋጁ እንዲቀመጥ አሳስበዋል፡፡

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ ዓዋጅ ፤ ዓዋጅ ቁጥር 1410/2018 አድርጎ በሁለት ተቃውሞ፤ በአብላጫ ድምፅ ማፅደቁን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል




ምክር ቤትሕግና ፍትሕየፖለቲካ ፓርቲዎችፖለቲካ

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!