እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:47:08 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ኢኮኖሚ

የግብርናውን ዘርፍ ለማሸጋገር የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ይስፋፋል

3 ደቂቃ ንባብ
የግብርናውን ዘርፍ ለማሸጋገር የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ይስፋፋል
ግብርና ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ከፍተኛ ውጭ ምንዛሪ ወጥቶባቸው በተለያዩ የልማት አጋሮች ድጋፍ የተገዙ የግብርና ሜካናይዜሽን መሣሪያዎችን፣ ተሽከርካሪዎችንና ኮምፒዩተሮችን ለክልሎች ድጋፍ አድርጓል፡፡
1 / 2

የኢትዮጵያ ግብርና በተለይም የእርሻ ልማት በኋላ ቀር አሰራሮችና ልምዶች ተቀፍድዶ የኖረ መሆኑ ይታወቃል፡፡በሬና ገበሬን ጠምዶ ከማረስ ያልወጣ፡፡ምርታማነቱ ከአምራቹ  ፍጆታ ፎቀቅ ያላለ ሆኖ ኖሯል፡፡አሁንም ከዚህ ዓይነት አመራረት ሙሉ በሙሉ አልተላቀቀም፡፡

ከአገሪቱ ሕዝብ አራት አምስተኛውን ይሽፍናል ተብሎ የሚገመተው አርሶ አደር በምግብ ራስን ለመቻል የተያዙ ግቦችን ለማሳካት አቅም የሚያንሰው ሆኖ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡

ባደጉ አገሮች በግብርና ሥራ የተሰማሩ ከ10 በመቶ የማይበልጡ አርሶ አደሮች ከአገራቸው አልፈው የሌሎችን አገሮች ሕዝብ የሚመግቡበት አቅም አዳብረዋል፡፡

የእርሻውን መስክ ላይ አተኮርን እንጂ፤ በእንስሳት ርባታ፣በዓሣ ሀብት፣ በንብ ማነብና በደን ሀብት አያያዝና አጠቃቀም  ዘርፎች ያለው ምርትና ምርታማነታችን ዝቅተኛ ሆኖ መኖሩን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግብርና ሥራዎችን በካይናዜሽን ለማልማትና አካባቢ ላይ  የተመሰረቱ ገበያ መር ምርቶችን ለማምረት የተጀመሩ አበረታች እንቅስቃሴዎች መታየት ጀምረዋል፡፡

አርሶና አርብቶ አደሩ የግብርና ምርቶቹን በዕውቀትና ዘመኑ ቴክኖሎጂና አስተሳሰብ በሚጠይቀው ሁኔታ በማምረት ከአገር ውስጥ ፎጆታ አልፎ፤ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

የአርሶና አርብቶ አደሮች ጥረት በግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍ እገዛ የሚያመረቃ ነው ማለት ይቻላል፡፡ጥረታቸው በውጤት ታጅቦ  ሕይወት ሲቀይር ይታያልና፡፡

መንግሥት የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ከመሠረቱ የሚያቀይሩ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮችና አመራረትን በስፋት ለማስተዋወቅና ለማስለመድ  ትኩረት ሰጥቷል፡፡

በየጊዜውም ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን ከውጭ ገዝቶ ወደ አገር ውስ በማስገባት ለክልሎች ያከፋፍላል፤ክልሎችም አርሶና አርብቶ አደሮች ተጠቅመውባቸው ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ያደርጋሉ፡፡

ግብርና ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ከፍተኛ ውጭ ምንዛሪ ወጥቶባቸው በተለያዩ የልማት አጋሮች ድጋፍ የተገዙ የግብርና ሜካናይዜሽን መሣሪያዎችን፣ ተሽከርካሪዎችንና ኮምፒዩተሮችን ለክልሎች ድጋፍ አድርጓል፡፡

የተሰራጩት የግብርና ሜካናይዜሽኖች፣ ተሸከርካሪዎችኮምፒዩተሮች 2ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው  መሆናቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከተከፋፈሉት ዘመናዊ መሣሪያዎች መካከል 134 ዘመናዊ ትራክተሮች ናቸው፡፡

እንዲሁም 150 የሩዝ ማቀነባበሪያ ማሽኖችና አምስት የከርሰ-ምድር ውሃ ማውጫ ማሽኖች በድጋፉ ተካተዋል፡፡

በተጨማሪም አራት ባለብዙ ደረጃ እንቁላል መታቀፊያዎችና የአንድ ደረጃ መፈልፈያ መሣሪያዎችና 460 በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ተከፋፍለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ 15 ተሸከረካሪዎችና 243 ሞተር ቢስክሌቶች እንዲሁም 980 ዴስከ ቶፕና ላፕ ቶፕ ኮምፒዩተሮች የድጋፉ አካል ሆነው ተሰራጭተዋል።

የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ በዚሁ ወቅት የግብርናውን ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂን ማስፋፋትና ተደራሽ ማድረግ አንዱ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽን የመንግሥት ዋነኛ ሰሶ በመሆኑ ዘርፉን ከተለመደው አሰራር በማውጣት አርሶና አርብቶ አደሩን፣ ሴቶችና ወጣቶችን የግብርና ሜካናይዜሽን ማስታጠቅ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ተናግረዋል፡፡

ግብርናው ገጠሩን የሚያንቀሳቅስ፣ ወጣቶችና ሴቶችን በስፋት የሚያሳትፍ በመሆኑ ይህን በግብርና ሜካናይዜሽን በመደገፍ ዘርፉን ከበሬ ጫንቃ ማላቀቅ ይገባናል በማለትም አሳሰበዋል፡፡

የግብርና ሜካናይዜሽን፣ የመስኖ ልማት፣ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ የባዮቴክኖሎጂ ትግበራ፣ የዶሮ ጫጩት አቅርቦትና ስርጭት፣ እንስሳት ጤናና መኖ ላይ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ በማመላከት፡፡

ለክልሎቹ የተሰጡት ማሽነሪዎች በአግባቡ ለታለመለት አገልግሎት በማዋል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ሚኒስትሩ አስገነዝበዋል፡፡

ግብርና ሚኒስቴር ባለፉት ዓመታተም በተመሳሳይ መንገድ ዘመናዊ ግብርና መገልገያ መሣሪያዎችን ለክልሎች በማከፋፈል የአገሪቱ ግብርና ልማት ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የግብርና መሣሪያዎቹን የአርሶና አርብቶ አደሩን ድካምና ጉልበት በመቆጠብ ከማስቻላቸውም በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠነ ሥራዎች በማከናወንና ጥራቱ የተጠበቀ ምርት ለማግኘት እንደሚያስችሉት በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ግብርና

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!