እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
05:10:16 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ኢኮኖሚ

የፈጣን መንገድ የክፍያና የቅጣት መክፈያ ሥርዓት ይፋ ተደረገ

2 ደቂቃ ንባብ
የፈጣን መንገድ የክፍያና የቅጣት መክፈያ ሥርዓት ይፋ ተደረገ

ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የፈጣን መንገድ የክፍያና የቅጣት መክፈያ ሥርዓት(ሶሉሽን) ዛሬ ይፋ አደረጉ።

የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱ በአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ሚና ባለው የአዲስ አበባ - አዳማ የፈጣን መንገድ ላይ የመንገድ አገልግሎትና የቅጣት ክፍያዎችን ለመፈጸም ያስችላል።

ለዚህም በቴሌብር ሱፐር አፕ አማካኝነት በዘመናዊ መንገድ የሚከናወንበት ዘዴ ተፈጥሮለታል፡፡

ቀደም ሲል በእጅ ንክኪና በጥሬ ገንዘብ ሲከናወን የነበረውን የፍጥነት መንገዶች ክፍያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመተካት ያስችላል ተብሏል።

ሥርዓቱ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ራዕይን ለማሳካትና የትራንስፖርት ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማዘመን እመርታ መሆኑም ተመላክቷል።

በቴሌብር ሱፐር አፕ ውስጥ የቀረበው አዲሱ የቶሎ (TOLO) አነስተኛ መተግበሪያ፤ አሽከርካሪዎች የተሽከርካሪዎቻቸውን መረጃ ጋር ከሚያገናኝ ሌላ ቴክኖሎጂ ጋር  ያገናኛል።

ይህንንም አሽከርካሪዎች ከቴሌብር አካውንታቸው ጋር በማስተሳሰር የፈጣን መንገድ ክፍያዎችን በራስ-አገዝ መንገድ እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል፡፡

ሥርዓቱ ክፍያውን በራስ-አገዝ መንገድ ተቀናሽ ስለሚደረግ፤ አሽከርካሪዎች በክፍያ በሮች ላይ መቆም ሳይጠበቅባቸው ጉዞአቸውን  በቅጽበት እንዲቀጥሉ የሚያስችል የላቀ ቴክኖሎጂ ነው፡፡

ይህ አዲሱ የዲጂታል አሠራር ቀደም ሲል የነበረውን አድካሚ የጥሬ ገንዘብ አሠራር በመተካት፤ በመግቢያና መውጫ በሮች ላይ የሚፈጠር የትራፊክ መጨናነቅና የጊዜ ብክነትን ያስቀራል።

ከዚህም በላይ ተገልጋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋልይላል የኢትዮ  ቴሌኮም መረጃ።

በተጨማሪም ኢንተርፕራይዙ ሥርዓቱነ ተጠቅሞ ሁሉንም የገቢ ምንጮቹን በቅጽበትና ግልጽነት ባለው መንገድ ለመቆጣጠር ያስችላል።

ስምምነቱ የቴሌብርን ተደራሽነት በመጠቀም የሥራ ቅልጥፍናንና የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ የላቀ ሚና እንደሚኖረውም ተገልጿል።

ኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ተቋማቸው ከመደበኛ የቴሌኮም አገልግሎት ባሻገር ፤ቀልጣፋ፣ምቹና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት በማቅረብ የፋይናንስ ዘርፉን እየደገፈ መሆኑንም  ተናግረዋል።

ሥርዓቱ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን የሚያሳልጥ መሆኑንም በመጠቆም።

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙስጠፋ አባሲመልኢንተርፕራይዙ በቀን ከ32 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግድ እንደመሆኑ፣ አዲሱ የ"ቶሎ" ዲጂታል ክፍያ አሠራር ጊዜን ከመቆጠብ ባሻገር፤ የአገልግሎት ጥራትንና የመንገድ ደኅንነት ቁጥጥርን ያሳድገዋል ብለዋል።

አዲሱን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት የሚጠቀሙ ደንበኞችን ለማበረታታት የ10 በመቶ የዋጋ ቅናሽ የተዘጋጀ ሲሆን፣  ማበረታቻው ደንበኞች ከጥሬ ገንዘብ ንክኪ ወጥተው ወደ ዘመናዊው አሠራር እንዲቀላቀሉ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ኢንተርፕራይዙ ባለፈው  በጀት ዓመት 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡንና በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው አጋማሽ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ማስገባቱን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር የሚገኘው  ተቋም፣ አገልግሎቱን 100 በመቶ ዲጂታል ለማድረግና አረንጓዴ ኢነርጂን ሥራ ላይ ለማዋል እየሰራ መሆኑም ተወስቷል።


ኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂዲጂታል ኢትዮጵያ

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!