እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
06:43:49 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ማህበራዊ

ገጠመኞች

2 ደቂቃ ንባብ
ገጠመኞች
የጽህፈት ቤቱን ኃላፊ ጨምሮ በቀዳሚው ዓመት ክፍያ ስፈጽም የተከፈተው ፋይል አንደሌለ ተነገረኝ።ቤቱም ቀደም ሲል(ስም ከመዞሩ በፊት በነበረው ግለሰብ ስም)እንደሚገኝ ተነግሮኝ ወጣሁ።በአጭሩ “ፋይሉ የለም”ተብዬ፤እኔም አንድአንድ ቀን ክፍያውን እንደምጠየቅ አምኜ ወደ መኖሪያዬ አዝኜ ተመለስኩ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጥቂት ዓመታት በፊት የደረሰኝን መኖሪያ የጋራ መኖሪያ ቤት(ኮንዶሚኒዬም)ባለቤት ነኝ፡፡ ከሌላ ሰው ተለዋውጬ(ባለ ሁለት መኝታ በባለ አንድ መኝታ)ነው፡፡ሆኖም ከኑሮና በሌሎች ምክንያቶች ለጊዜው አልኖርበትም፤ ቤቴን አከራይቼ አኔም ተከራይቼ እኖራለሁ።

ባለፈው ዓመት በራሴ ስም የማዞር፣ያለበትን ዕዳ የመከፈልና የመኖሪያ ቤት ኪራይ፣ቁጥጥርና አስተዳደር ዓዋጅ ቁጥር1320/2016በሚያዘው መሠረት የአከራይ ተከራይ ክፍያ በወረዳ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ቀርቤ ከፈልኩ።ዓመታዊ ግብር(ጣሪያና ግድግዳ የሚባለውን)አካትቼ ሳከናውን ቆየሁ።

ዘንድሮ በ2017 የቤቱ ሙሉ ባለቤትነት ያረጋገጥኩበት በመሆኑ በስሜ ዓመታዊ ግብር ክፍያ ፈጸምኩ።በተጓዳኝ ቤቴ በተከራይ እጅ በመሆኑ የአከራይ ተከራይ ክፍያ በመክፈል ግዴታዬን ለመወጣት ለጽህፈት ቤቱ ጥያቄዬን አቀረብኩ።

እንግዲህ እዚህ ላይ ነው ድራማው የሚጀምረው።የጽህፈት ቤቱን ኃላፊ ጨምሮ በቀዳሚው ዓመት ክፍያ ስፈጽም የተከፈተው ፋይል አንደሌለ ተነገረኝ።ቤቱም ቀደም ሲል(ስም ከመዞሩ በፊት በነበረው ግለሰብ ስም)እንደሚገኝ ተነግሮኝ ወጣሁ።በአጭሩ “ፋይሉ የለም”ተብዬ፤እኔም አንድአንድ ቀን ክፍያውን እንደምጠየቅ አምኜ ወደ መኖሪያዬ አዝኜ ተመለስኩ።

ከአራት ወራት በኋላ ባከራየሁት በራፍ ላይ ያልተከፈለ የኪራይ ተከራይ ዕዳ እንዳለብኝ ፣ በተደጋጋሚ ተፈልጌ እንዳልተገኘሁ፣አመጸኛና አስቸጋሪ ቢጤ መሆኑን የሚያትትና በሦስት ቀናት ውስጥ ብር 12ሺህ735ከ95 እንድከፍል የሚጠይቅ ይሄንን ካላደረግኩኝ ጉዳዬ በሕግ እንደሚቀርብ የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ባከራየሁት ቤት ተለጠፈ።

ማስጠንቀቂያው በተለጠፈ ማግስት ወደ ጽህፈት ቤቱ ሄጄ ጉዳዬን ከያዙት ባለሙያ ጋር በጥቅምት ወር ክፍያውን ለመፈጸም ጠይቄ እንደነበር ለማስታወስ ሞከርኩ፤የተረፈኝ ነገር ትናንትህን እርሳው ዓይነት በመሆኑ ክፍያውን ያለ መቀጮ ለመክፈል መቅረቤን አሳወቅኩኝ።ሆኖም ምንነቱን ያልተረዳሁት ተጨማሪ ብር 868ከ79ሣንቲም ታክሎበት በጠቅላላው ብር 13ሺህ 604ከ61ሣንቲም በኢትዮጵያ ንግድ ባንከ ገቢ በኩል ገቢ አደረግኩኝ።

ክፍያወ ፈጽሜ፤ግዴታዬን ብወጣም ጽህፈት ቤቱ ሦስት ጉዳዮችን እንዳነሳበት ያስገድደኛል።አንደኛ የዜግነት ግዴታዬን ልወጣ ብሎ ዜጋን”ፋይል የለህም”ብሎ መመለስ ተገባ ነወይ?

ሁለተኛ ግብር ከፋዩን ለማግኘት ጥረት ምንም ጥረት ባልተደረገበት ሁኔታ “በተደጋጋሚ ሙከራ ተደርጎ”ና “ፈቃደኛ ባለመሆንዎ” ብሎ በታማኝነትና በቅንነት ግዴታውን ለመወጣት የቀረበ ዜጋን ማስፈራራት ተገቢ ነው?

ሦስተኛ በማስጠንቀቂያ ማስታወቂያው ላይ የተጠቀሰውን የግብር መጠን በሦስት ቀናት ውሰጥ እንዲከፍል የተጠየቀ ግብር ከፋይ ማስጠንቀቂያው በተሰጠ ማግስት ለክፍያ ሲቀርብ በብልጫ አንዲከፍል ማድረግ(ፍርድ ቤት ቀርቦ ቅጣት ሳይወሰንበት)ምን ያህል ሕጋዊ ነው?

እኔ የገጠመኝ ጉዳይ ግብርን በተለይ የአከራይ ተከራይ ክፍያ በራስ አሳውቆ መክፈል ችግር ነው፤ጽህፈት ቤቱ ባሻው ጊዜ ወንጅሎና ስም አጥፍቶ ሒሳቡንም ከጠየቀው በላይ አድርጎ ለማስከፈል ግን ባለ ሙሉ መብት ነው።በዚህ ዓይነት የሚከፈል የዜጎችን መብት በመደፍጠጥ የሚሰበሰብ ኪራይና ከፋዩንም አማራሪ ይሆናል። ሕግና ሥርዓት ተከብሮና ግብሩን ለማስገባት ጥረት ሳይደረግ ከውንጀላ ጋር ግብር ማስከፈል ተገቢ አይደለም እላለሁ፡፡

 

 

ገጠመኞች

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!